ሳዑዲ አረቢያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ የአውሮፓውያኑን አዲስ ዓመትን ልታከብር ነው
ሳዑዲ የአውሮፓውያኑን አዲስ ዓመት 2020 ማክበር የጀመረች ሲሆን ይሄም በታሪኳ የመጀመሪያዋ ነው፡፡
2020 እስኪደርስ በቀሩት ቀናት የሰዓታት እና ደቁቃዎች ቆጠራን በማድረግ፣ ደማቅ ርችት በማዘጋጀት፣ የሙዚቃ ድግስ እና መሰል ክዋኔዎችን በመከወን በዓሉን በድምቀት ለማክበር ሀገሪቱ ዝግጅት አድርጋለች እንደ አረቢያ ድረ-ገጽ ዘገባ፡፡
ከሀገሪቱ መንግስት ያልተጠበቁ አስገራሚ ውሳኔዎች (ሰርፕራይዝም) ከአዲስ ዓመት ጋር በተያያዘ ሊኖር እንደሚችል ይጠበቃል፡፡
የሳዑዲ ዜጎች በሀገራቸው ይሆናል ብለው አስበው የማያውቁትን የአዲስ ዓመት በዓል ለማክበር የፈረንጆቹን የታህሳስ ወር የመጨረሻ ቀን የመጨረ ሰዓታት በጉጉት በመጠባበቅ ላይ ናቸው፡፡ በዓሉ በአውሮፓውያኑ ታህሳስ 31 ከለሊቱ ስድስት ሰዓት ጀምሮ እስከንጋት በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል ነው የተባለው፡፡
በሳዑዲ ከዚህ ቀደም የአውሮፓውያኑን አዲስ ዓመት ማክበር በጥብቅ የተከለከለ እና በዓሉን ማክበር ለቅጣት የሚዳርግ ሲሆን ሀገሪቱ የምታከብረው ኢስላማዊውን የሂጅራ አዲስ ዓመት ነው፡፡
አሁን ላይ አለማቀፉ የአውሮፓውያን አዲስ ዓመት ሊከበር የቻለው የሀገቱ ልዑል ሞሀመድ ቢን ሳልማን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገሪቱ ሁለንተናዊ ለውጥ ለማምታት ሪፎርም እያደረጉ በሚገኙበት ወቅት ነው፡፡
በርካታ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሪፎርሞችን በማድረግ ላይ የሚገኙት ልዑሉ ከዚህ ቀደም ክልክል የነበሩ የተለያዩ ተግባራትን መቀየራቸው ይታወቃል፡፡