ኢራን ዛሬ በተገደሉት የጦር መሪ ቦታ አዲስ ጄነራል ሾመች
አሜሪካ በባግዳድ በወሰደችው የአየር ጥቃት የኢራን የጦር መሪ ቃሲም ሶሌይማኒ መገደላቸውን ተከትሎ፣ የሀገሪቱ መንፈሳዊ መሪ አያቶላ አል ካሚኒ ጄነራል ኢስማኤል ቃኒን መተካታቸውን አሳውቀዋል፡፡
ዛሬ ታህሳስ 24 ቀን 2012 ዓ.ም. የተገደሉት ቃሲም ሶሌይማኒ ከአያቶላ አል ካሚኒ ቀጥሎ ሁለተኛ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰው እንደሆኑ ይነገርላቸል፡፡
አሜሪካ በባግዳድ በሚገኘው ኤምባሲዋ ላይ በሰልፈኞች የተቃጣውን ጥቃት ተከትሎ ኢራንን ስትወነጅል ነበር፡፡ 750 የሚሆኑ ወታደሮቿንም ወደ ኢራቅ ልካለች፡፡
ጄነራል ቃሲም ሶሌይማኒ በባግዳድ አየር ማረፊያ አቅራቢያ በመኪና ሲንቀሳቀሱ በነበሩበት ወቅት በአሜሪካ ጥቃት የተገደሉ ሲሆን የአሜሪካ የመከላከያ መሥሪያ ቤት፣ ፔንታጎን፣ ጄነራሉ የተገደሉት በፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ትዕዛዝ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ዛሬ የተፈፀመውን ግድያ ተከትሎ ኢራን የበቀል እርምጃ እንደምትወስድ አስታውቃለች፡፡
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ በትዊተር ገፃቸው፣ አሜሪካ ግጭት ለማርገብ ትሰራለች ቢሉም በባግዳድ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በኢራን ያሉ የአሜሪካ ዜጎች ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ አሳስቧል፡፡
በሰዓታት ልዩነትም በባስራ ከተማ በነዳጅ ድርጅቶች ውስጥ የሚሰሩ የአሜሪካ ዜጎች ስራ አቁመው ወደ ሀገራቸው ለመሄድ እየተሰናዱ መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የኢራቅ ባለስልጣናት ሁኔታው በነዳጅ ምርት ላይ የሚፈጥረው ጫና እንደማይኖር አሳውቀዋል፡፡
ይሁን እንጂ በዛሬው ዕለት ብቻ የአንድ በርሜል ነዳጅ ዋጋ በ2 ዶላር ጭማሪ አሳይቷል፡፡
ኢራቅ ነዳጅን በብዛት ወደ ውጭ ከሚልኩ ኦፔክ (OPEC) ሀገራት ሁለተኛዋ ስትሆን በቀን 4.62 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ ለዓለም ገበያ ታቀርባለች፡፡
ምንጭ፡-ሮይተርስ