ደቡብ ኮሪያ፣ ጃፓንና ቻይና አሜሪካና ሰሜን ኮሪያ ዳግም እንዲነጋገሩ ሊያደርጉ ነው
ሴኡል፣ ቶኪዮና ቤጂንግ ዋሸንግተንና ፒዮንግያንግ እንዲወያዩና በመካላቸው ያለው ችግር እንዲፈታ ለማድረግ መስማማታች ተሰምቷል፡፡
ሦስቱ ሀገሮች በቻይ በነበራቸው ጉባዔ በሁለቱ አገሮች መካከል ንግግር እንዲጀመር ለማድርግ መስማማታቸውን የደቡብ ኮሪያው ፕሬዚዳንት ሙን ጃኢን አስታውቀዋል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዚዳን ዶናልድ ትራምፕና የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን በተደጋጋሚ ቢገናኙም ንግግራቸው ግን ካለውጤት መጠናቀቁ ይታወሳል፡፡
በደቡብ ምዕራቧ የቻይና ከተማ የተገናኙት የቻይናው ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኬኪያንግ፣ የጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ሽንዞ አቤና የደቡብ ኮሪያው ፕሬዚዳንት ሙን ጃ ኢን በዋሸንግተንና በፒዮንግያንግ መካከል ተግባቦት እንዲኖር አንሰራለን በማለት ነው የተስማሙት፡፡
ዋነኛ የንግግር ማጠንጠኛዎች ይሆናሉ የተባሉት ደግሞ የኒዩክለር መርሃ ግብርና ዘላቂ ሰላም እንደሚሆኑ ነው ከውይይቱ በኋላ የተገለጸው፡፡
የሶስቱም አገራት መሪዎች በጋራ በሰጡት መግለጫ በኮሪያ ልሳነ ምድር ሰላም እንዲሰፍን በጋራ እንሰራለን ብለዋል፡፡ በአካባቢው ሰላም እንደሚያስፈልግ እናምናለን ያሉት መሪዎቹ በዋናነት ይህ ሰላም የሚመጣው ደግሞ ንግግሮችና ውይይቶች ሲደረጉ ነው ብለዋል፡፡
ቻይና የሰሜን ኮሪያ ዋነኛ የንግድ አጋር ብትሆንም ከሰሞኑ ግን ፒዮንግያንግ የሚሳኤልና የኒዩክለር ሙከራ ማድረጓ ቤጂንግን አስቆጠቷል፡፡
በሰሜን ኮሪያ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ስቴቨን ቤይጉን በቻይና ባደረጉት የሁለት ቀናት ጉብኝት ከቻይና ከፍተኛ ዲፕሎማቶች ጋር ተነጋግረዋል፡፡
ቀደም ሲል በሰሜን ኮሪያ ላይ የተጣሉ ማዕቀቦች እንዲነሱ ቻይና ከሩሲያ ጋር ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ሰነድ ማቅረቧ ይታወቃል፡፡ ይሄም ቻይና ከወዳጇ ሰሜን ኮሪያ ጋር ያላት ወዳጅነት እንዳይቀዘቅዝባት በመስጋት ያደረገችው ነው፡፡
ምንጭ፡- ኤዥያን ሪቪው