በሶሪያ ኢድሊብ በትንሹ 33 የቱርክ ወታደሮች በአየር ጥቃት ተገደሉ
በሶሪያ ኢድሊብ በትንሹ 33 የቱርክ ወታደሮች በአየር ጥቃት ተገደሉ
በሶሪያ ኢድሊብ ግዛት ትናንት ምሽት የሀገሪቱ መንግስት ፈጸመ በተባለ የአየር ጥቃት በትንሹ 33 የቱርክ ወታደሮች መገደላቸውን ቱርክ አስታውቃለች፡፡ በጥቃቱ 35 ተጨማሪ ወታደሮች ተጎድተዋል፡፡
ጥቃቱ የተፈጸመው የሶሪያ መንግስት ወታደሮች በቅርብ ወራት ከአማጺያን የነጠቋቸውን ይዞታዎች ለቀው እንዲወጡ ቱርክ ያስቀመጠችው ቀነ ገደብ ከመጠናቀቁ ከቀናት በፊት ነው፡፡
ቱርክ ለብሄራዊ ደህንነቴ ባዘመትኳቸው ጀግና ወታደሮች ላይ የተፈጸመ ትልቅ ወንጀል ስትል ጥቃቱን አጣጥላለች፡፡ክስተቱን ተከትሎ የቱርክ ባለስልጣናት በፕሬዝዳንቱ ቤተ-መንግስት ስብሰባ አድርገው ሀገሪቱ የበቀል እርምጃ መውሰዷን የቱርክ ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር ፋሬቲን አልቱን ገልጸዋል፡፡ ሀገሪቱ በአጸፋው 200 የሶሪያ መንግስት ኢላማዎችን መደብደቧን አስታውቃለች፡፡
የሶሪያ መንግስት ቀኝ እጅ የሆነችው ሩሲያ፣ ቱርካዊያን ወታደሮች የተመቱት በኢድሊብ ግዛት ከጂሃዲስቶች ጋር ሲያብሩ ነው ብላለች፡፡
ክስተቱ ሶሪያና ኢራንን ወደ ለየለት ግጭት እንዳያማራቸው የአውሮፓ ህብረት ስጋቱን ገልጿል፡፡ ከዚህም ባለፈ የአካባቢውን ሰብአዊ ቀውስ ይበልጥ ያወሳስበዋል ሲሉ የህብረቱ የውጭ ፖሊሲ ኃላፊ ጆሴፍ ቦሬል ትዊት አድርገዋል፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ በስልክ ውይይት ያደረጉት የቱርክና ሩሲያ ፕሬዝዳንቶች ችግሩን ለማርገብ የሚያስችሉ እርምጃዎችን ለመውሰድ ተስማምተዋል፡፡ የሁለቱ ሀገራት ባለስልጣናት በቱርክ አንካራ ተገናኝተው ውይይት እንደሚያደርጉም ተጠቁሟል፡፡
በሶሪያ በኩል ተፈጸመ ስለተባለው ጥቃት እና ስለደረሰው ጉዳት ምንም የተባለ ነገር የለም፡፡
የሶሪያ አማጽያንን የምትደግፈው ቱርክ በሶሪያ ኢድሊብ ግዛት በሚገኘው የአማጽያኑ የመጨረሻ ይዞታ ላይ ወታደሮቿ ይገኛሉ፡፡
ቱርክ ከጥቃቱ ጋር በተያያዘ የምክር አገልግሎት መጠየቋን ተከትሎ የሰሜን ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (NATO) ምክር ቤት አባላትም ዛሬ ስብሰባ ይቀመጣሉ ሲል ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡