የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ ለፓኪስታን 200 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አደረገች
የአቡ ዳቢ ዘውዳዊ ልዑል እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ ጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ አዛዥ ሼክ መሀመድ ቢን ዘይድ አል ነህያን በፓስታን ያደረጉትን ጉብኝት ሲያጠናቅቁ ሀገራቸው ለፓኪስታን 200 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደምታደርግ ገልጸዋል፡፡
ፓኪስታን በድጋፍ ያገኘችው ይህ ገንዘብ የሀገሪቱን አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ለመደገፍ ያለመ ነው ተብሏል፡፡
ሼክ መሀመድ ቢን ዘይድ አል ነህያን በፓኪስታን መዲና ኢስላማባድ ከትናንት ታህሳስ 23 ቀን 2012 ዓ.ም. ሀሙስ ጀምሮ በነበራቸው የሁለት ቀናት ጉብኝት ከሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር በበርካታ ጉዳችች ላይ መወያየታቸው ተሰምቷል፡፡
ከጠቅላይ ሚኒስትር ኢምራን ካሃን ጋር በነበራቸው ውይይት በዋናነትም የሁለትዮሽ ቀጣናዊና ዓለማቀፋዊ ጉዳችች ላይ መመካከራቸው ነው የተዘገበው፡፡
ሼክ መሀመድ ቢን ዘይድ አል ነህያን የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ ከፓኪስታን ጋር ያላትን ወዳጅነት አጠናክራ እንደምትቀጥል በውይይቱ ወቅት አረጋግጠዋል፡፡
ፓኪሰታን በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር እየተጫወተች ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑንም ነው ሼክ መሀመድ ቢን ዘይድ የገለጹት፡፡ በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ ቀጣይ ድጋፍ እንደምተደርግም ልዑሉ ቃል ገብተዋል፡፡
ሁለቱ ሀገሮች በታሪክ፣ በባህል እና በማህበራዊ መስኮች በጋራ ለመስራትም ተስማምተዋል ተብሏል፡፡
ሼክ መሀመድ ቢን ዘይድ አል ነህያን በፈረንጆቹ 2020 ፓኪሰታንን የጎበኙ የመጀመሪያው ከፍተኛ ባለስልጣን ናቸው፡፡