የዩክሬን አይሮፕላን ኢራን ላይ ተከስክሶ 176 ሰዎች ሞቱ
176 ሰዎችን አሳፍሮ ሲጓዝ የነበረው የዩክሬን ዓለማቀፍ አየር መንገድ ንብረት የሆነው ቦይንግ 737 ፕሌን ዛሬ ረቡዕ ታህሳስ 29 ቀን 2012 ዓ.ም ማለዳ ላይ ከቴህራን አየር ማረፊያ በተነሳ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ተከስክሶ ያሳፈራቸው ሰዎች በሙሉ በአደጋው ሞተዋል፡፡ በፕሌኑ ላይ ከነበሩ ተጓዦች ዘጠኑ የበረራ ሰራተኞች ናቸው፡፡
የዩክሬን ሚዲያዎች ቀደም ብለው ባወጡት ሪፖርት ተሳፋሪዎቹ 180 እንደነበሩ ዘግበው ነበር፡፡
ፕሌኑ ከኢራን ተነስቶ ወደ ዩክሬን፣ ኬቭ በመብረር ላይ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ፐሌኑ ወደተከሰከሰበት ስፍራ አምርተው ስራ ቢጀምሩም የአካባቢው ነበልባል ግን በፍጥነት ወደ ተግባር ለመግባት እንዳላስቻላቸው የሲኤንኤን መረጃ ያመለክታል፡፡
የተከሰከሰው ፕሌን አራት ዓመት ተኩል የአገልግሎት እድሜ ያለው ነው፡፡ የመከስከሱ ምክኒያት የቴክኒክ ችግር እንደነ የኢራን ሚያዎች ዘግበዋል፡፡ ይሁን እንጂ የቦይንግ ቃል አቀባይ ኩባንያው መረጃዎችን ገና በማሰባሰብ ላይ እንደሚገኝ ነው የተናገሩት፡፡
አደጋው የተከሰተው ከሳምንታት በፊት ከኃላፊነት የተነሱትን የቦይንግ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዴኒስ ሙሊንበርግን በመተካት የተሰየሙት ዴቪድ ካልሆን ስራቸውን በይፋ ለመጀመር በመንደርደር ላይ ባሉበት ወቅት ነው፡፡
ግዙፉ የአሜሪካ አቪዬሽን ኩባንያ-ቦይንግ 346 ሰዎች የሞቱበት ሁለት የ737 ማክስ አይሮፕላኖች አደጋ ከተከሰተ ወዲህ ፈተና ውስጥ መግባቱ ይታወቃል፡፡ በኢንዶኔዢያው ላዮን ኤይር እና በኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ ከተከሰቱት ከነዚህ አደጋዎች በኋላ በመላው ዓለም የ737 ማክስ አይሮፕላኖች ከስራ ውጭ መደረጋቸው ይታወሳል፡፡
ምንጭ፡- ሲኤንኤን