ጄነራል ሱሌይማኒ የሦስተኛው ዓለም ጦርነት ቀስቃሽ ምክኒያት ይሆኑን?
ሰሞነኛው የፐርሽያ አካባቢ ውጥረት የዓለም ፖለቲከኞችና መገናኛ ብዙሃን መነጋሪያ ሆኖ ቆይቷል፡፡
ጉዳዩ ከዚህ በኋላም መነጋገሪያና መወያያ የመሆን ዕድሉ ከፍተኛ እንደሆነ እየተገለጸ ነው፡፡
ከኢራኑ መንፈሳዊ መሪ አያቶላ ሃሚኒ ቀጥሎ ትልቁና ተፈሪው የኢራን ሰው ቃሲም ሱሌይማኒ በአሜሪካ መገደላቸው ዋሸንግተንንና ቴህራንን ቀድሞ ከነበረው ባላንጣነታቸው በባሰ ሁኔታ ብዙ አነጋግሯቸዋል፡፡
የጄነራል ሱሌይማኒ ግዲያ ከግለሰብም በላይ መሆኑን የሚገልጹት ተንታኞች በአሜሪካና ኢራን መካከል ያለው ባላንጣነት እንደሚብስበትም እየተናገሩ ነው፡፡
ኢራን ከጄነራሏ ግዲያ በኋላ አጸፋዊ ምላሽ አሰጣለሁ ማለቷ የሚታወስ ሲሆን በኢራቅ የአሜሪካ 2 ጦር ሰፈሮች ላይ ጥቃት መፈጸሟንና ኪሳራ ማድረሷን ስትገልጽ ቆይታለች፡፡
ከዚህ የኢራን ድርጊት ቀጥሎ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተጠባቂ የነበረውን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
የኢራኑ ጄነራል ቃሲም ሱሌይማኒ ግዲያ ትክክልና ወቅታዊ እንደነበር እንዲያዉም ቀደም ብለው መገደል እንደነበረባቸው ፕሬዝዳንቱ በመግለጫቸው ተናገሩ፡፡
ከዚህ ባለፈም ቃሲም ሱሌይማኒ በመካከለኛው ምስራቅ ለበርካቶች ሞት ምክንያት እደነበሩ ዶናልድ ትራምፕ ተናግረዋል፡፡
ኢራን ሽብር ከሚደግፉ አገሮች ተርታ ትሰለፋለች ያሉት ፕሬዚዳንት ትራምፕ ኢራን አጸፋ ባለችው ጥቃት ከአነስተኛ ጉዳት ባለፈ ከፍተኛ ጉዳት አለመድረሱንና ኢራቃውያንም ሆኑ አሜሪካውያን አለመገደላቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡
ከሰሞኑ የኢራኑ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሐመድ ጃቫድ ዛሪፍ ደግሞ አሜሪካ እንዳልገባ ተከልክያለሁ ማለታቸው የሚታወስ ነው፡፡
በአሜሪካና ኢራን መሪዎች እየተሰጡ ያሉ መግለጫዎች ዓለምን ለተጨማሪ ጦርነት ብሎም ኪሳራ እንዳይጋብዝ የበርካቶች ስጋትና ጸሎት ሆኗል፡፡
ያም ሆነ ይህ የሁለቱ አገራት እሰጥ አገባ ከቃላት ጦርነት ያለፈ ነውና ስጋቱ ከዜጎች ደህንነት አስከ ጦር መሳሪያ ፍጭት ከዚያም እስከ ነዳጅ ዋጋ ማሻቀብ የሚደርስ ዳፋ እንደሚኖረው ይገመታል፡፡
አንዳንድ መገናኛ ብዙሃንም አሁን ላይ በነዳጅ ላይ መጠነኛ የዋጋ ጭማሪ መከሰቱን እየዘገቡ ናቸው፡፡
በርካቶች አሜሪካም ኢራንም በውጊያ አቋማቸው እንዳይቀጥሉ ጥሪ ማቅረብ ጀምረዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ማኑኤል ኦሊቬራ ጉቴሬዝ፣ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ቻይናና ሌሎችም ውጥረቱ እንዳይባባስ ጠይቃዋል፡፡
አሁን ደግሞ ዋሽንግተን ከቴህራን ጋር ለመወያት ፍላጎት እንዳላት እየገለጸች ነው፡፡
ከአሜሪካ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተላከው ደብዳቤ እንደሚያመለክተው፣ አገሪቱ ከኢራን ጋር ለመነጋገር ቅድመ ሁኔታ አናስቀምጥም ብላለች፡፡
ደብዳቤውም የቃሲም ሱሌይማኒ ግዲያ ራስን የመከላከል አንዱ መንገድ ነው ይላል፡፡
የተገደሉት የኢራን ጄነራል አገራቸው በመካከለኛው ምስራቅ ያላትን ፖሊሲ ያዘጋጁ ጉልህ ሰው በሚል ይታወቃሉ የሚል ይዘትም አለው፡፡
ኢራን በኢራቅ በሚገኘው የአሜሪካ ጦር ሰፈር ላይ ያደረስኩት ጥቃት አሜሪካ በቀጣናው ያላት ሚና እንዲያበቃ የሚያደርግ ነው ብላለች፡፡
አሜሪካ ለዓለም አቀፍ ሰላምና ደህንነት ሲባል ከኢራን ጋር ትደራደራለች ያሉት በመንግስታቱ ድርጅት የአሜሪካ አምባሳደር ኬሊ ክራፍት ለንግግር ቅድመ ሁኔታ አናስቀምጥም ብለዋል፡፡
አሁን ላይ አሜሪካ ካለምንም ቅድመ ሁኔታ እደራደራለሁ ማለቷ የትራምፕ አስተዳደር መለሳለስን ያሳያል የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡
ኢራንም አሜሪካ ወደ 2015 የኒዩክለር ስምምነት ለመመለስ ካሰበች የባለብዙ ወገን ንግግሮች ላይ መሳተፍ አለባት ብላለች፡፡
በፈረንጆቹ አዲስ ዓመት መባቻ የተጀመረውና ሃይልን የቀላቀለው የዋሸንግተንና ቴህራን እሰጥ አገባ ዓለም ሊያስታውሰው ወደ ማይፈልገው ጦርነት እንዳያመራ ተፈርቷል፡፡
ጉዳዩ በንግግርና በስምምነት ይፈታ ዘንድም አገራትና ዲፕሎማቶች እየወተወቱ ነው፡፡
ምንጭ፡-ሮይተርስ፣ሲኤንኤን