የዓለም ባንክ ለታንዛኒያ ሊያደርግ የነበረውን ብድር አራዘመ
የዓለም ባንክ ለታንዛኒያ የ500 ሚሊዮን ዶላር ብድር ለመስጠት ጫፍ ደርሶ የነበረ ቢሆንም በሀገሪቱ ያሉ አክቲቪስቶች ያነሱትን ተቃውሞ ታሳቢ በማድረግ የብድር ውሳኔውን አዘግይቷል፡፡
ብድሩ በዋናነት በተማሪነታቸው የሚያረግዙ ሴቶች ከወሊድ በኋላ ከመደበኛ ውጭ ባሉ ትምህርቶች ላይ የሚያደርጉትን ተሳትፎ ለማገዝ የሚውል ነው፡፡
የታንዛኒያ ህግ በትምህርት ላይ ያሉ ሴቶች ከወሊድ በኋላ ተመልሰው ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ አይፈቅድም፡፡
ነገር ግን ከመደበኛው ውጭ ባሉ አጫጭር ስልጠናዎች እንዲሳተፉ ይደረጋል፡፡ በሀገሪቱ ያሉ አክቲቪስቶችም ይህንን አሰራር በገንዘብ መደገፍ ሴቶችን የሚያገለውን ፖሊሲ መደገፍ ነው ስለዚህ የዓለም ባንክ ብድሩን መስጠት የለበትም ሲሉ ለተቋሙ መልዕክት አድርሰዋል፡፡
የዓለም ባንክም ዛሬ በብድሩ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ይዞት የነበረውን ቀጠሮ አራዝሟል፡፡
የታንዛኒያ ፕሬዚዳንት ጆን ማጉፉሊ የተነሳውን ትችት ወደ ጎን መተው ያስፈልጋል ብለው የዓለም ባንክ አቋማችንንና ስራችንን ስለሚያውቅ ብድሩን ይሰጠናል ብለዋል፡፡ ተቃዋሚዎችን ሁከት ፈጣሪዎች ሲሉም ወርፈዋል፡፡
በታንዛኒያ በ2017 ብቻ 5 ሺ 500 ሴት ተማሪዎች በእርግዝና ምክንያት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዲያቋርጡ ተደርጓል፡፡
በ2018 የዓለም ባንክ ለሀገሪቱ ሊሰጥ የነበረውን የ300 ሚሊዮን ዶላር ብድርም በዚሁ ነፍሰጡር ተማሪዎችን በትምህርት ገበታቸው እንዳይገኙ በሚያግደው ፖሊሲ ምክንያት ተመላሽ አድርጎታል፡፡
ምንጭ፡-ቢቢሲ