በጀኔቫ በተካሄደው ለኢትዮጵያዊያን እርዳታ ማሰባሰብ ፕሮግራም 630 ሚሊዮን ዶላር ተዋጣ
በፕሮግራሙ ላይ 21 ሀገራት ለኢትዮጵያ እርዳታ ለመስጠት ቃል ገብተዋል
በኢትዮጵያ ከ15 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ተመድ አስታውቋል
በጀኔቫ በተካሄደው ለኢትዮጵያዊያን እርዳታ ማሰባሰብ ፕሮግራም 630 ሚሊዮን ዶላር ተዋጣ።
በኢትዮጵያ በጦርነት እና አየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመርዳት በሚል የገንዘብ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም በስዊዘርላንድ ጀኔቫ ተካሂዷል።
አንድ ቢሊዮን ዶላር እርዳታ ለማሰባሰብ ተብሎ የተጀመረው ይህ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ላይ 15 ሀገራት ገንዘብ ለመስጠት ቃል ገብተዋል።
አሜሪካ በፕሮግራሙ ላይ 154 ሚሊዮን ዶላር፣ ብሪታንያ 124 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም የአውሮፓ ህብረት 139 ሚሊዮን ዶላር ለኢትዮጵያ እንደሚሰጡ ቃል ከገቡ ሀገራት መካከል ዋነኞቹ ናቸው።
በተመድ ዋና ጽህፈት ቢሮ የሰብዓዊ ድጋፍ አስተባባሪ የሆኑት ጆይስ ምሱያ እንዳሉት ይህ ጅማሮ ነው በቀጣዮቹ ወራት ተጨማሪ ድጋፍ ሊገኝ እንደሚችል ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ በጦርነት ፣ አየር ንብረት ለውጥ እና ሌሎች ምክንያቶች ለእርዳታ የተጋለጡ ዜጎች ቁጥር 15 ነጥብ 5 ሚሊዮን ደርሷል።
በአፋር፣ ትግራይ እና አማራ ክልሎች ደግሞ የምግብ ዕጥረቱ የከፋ ደረጃ ከመሆኑ ባለፈ ረሀብ በሚባል ሁኔታ ላይ እንደደረሰ ተመድ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ አደጋ እና ዝግጁነት ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም በመድረኩ ላይ እንዳሉት ዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች ለእርዳታ የተጋለጡ ዜጎች ወደ ተባባሰ ጉዳት ከመዳረጋቸው በፊት ተጨማሪ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
ኮሮና ቫይረስ፣ አንበጣ፣ የአየር ንብረት እና ሌሎች አደጋዎች በኢትዮጵያ ለእርዳታ የተጋለጡ ዜጎች ቁጥር እንዲጨምር ምክንያት መሆኑንም ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።
ተመድ በበኩሉ ከቀጣዩ ሀምሌ እስከ መስከረም ወር ድረስ ያለው ጊዜ ለኢትዮጵያ ከባድ ጊዜ ሊሆን እንደሚችል አስጠንቅቋል።
በኢትዮጵያ 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎች ከመኖሪያ ቀዬአቸው ተፈናቅለዋል የተባለ ሲሆን ይህም ኢትዮጵያ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ከፍተኛ ከሆነባቸው ሀገራት መካከል አንዷ እንዳደረጋት የተመድ ሪፖርት ያስረዳል።
በአጠቃላይ በኢትዮጵያ በቀጣዮቹ ሶስት ወራት ውስጥ ለተረጂዎች ድጋፍ ለማድረግ አንድ ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ተገልጿል።