አሜሪካ በሀገሯ በጊዜያዊነት ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ተጨማሪ የመኖሪያ ጊዜ ፈቀደች
በጊዜያዊነት ወደ አሜሪካ የገቡ ኢትዮጵያዊያን ለተጨማሪ 18 ወራት እንዲኖሩ ፈቃድ አግኝተዋል
አሜሪካ በአማራ እና ኦሮሚያ ያለው የሰብዓዊ መብት ጥሰትን እንደ ምክንያት ጠቅሳለች
አሜሪካ በሀገሯ ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ተጨማሪ የመኖሪያ ጊዜ ፈቀደች፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በነበረበት ወቅት ወደ አሜሪካ በጊዜያዊነት የገቡ ኢትዮጵያዊያን ለ18 ወራት እንዲቆዩ የመኖሪያ ፈቃድ ሰጥታ ነበር፡፡
ለአጭር ጊዜ ቪዛ አግኝተው ለጉብኝት፣ ትምህርት እና ሌሎች ምክንያቶች ወደ አሜሪካ የገቡ ኢትዮጵያዊያን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ እንደሚቸገሩ በወቅቱ አመልክተው ነበር፡፡
አሜሪካም ከኢትዮጵያዊያኑ ሀገራችን ጦርነት እና ሌሎች የፖለቲካ ቀውስ ላይ በመሆኗ ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ እንቸገራለን በሚል ለቀረበላት ጥያቄ ለ18 ወራት መኖር እንደሚሉ የመኖሪያ ፈቃድ ሰጥታ ነበር፡፡
ለነዚህ ኢትዮጵያዊያን አመልካቾች የተሰጠው የ18 ወራት ጊዜ የፊታችን ሰኔ ላይ የሚያበቃ የነበረ ሲሆን እነዚህ በጊዜያዊነት ይኖሩ የነበሩ ዜጎች ለተጨማሪ 18 ወራት እንዲኖሩ እንደተፈቀደላቸው ተገልጿል፡፡
የሀገሪቱ የሀገር ውስጥ ደህንነት ቢሮ ባወጣው መግለጫ በኢትዮጵያ አሁንም በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በመኖራቸው ምክንያት ለአጭር ጊዜ ወደ አሜሪካ የመጡ ኢትዮጵያዊያን ለተጨማሪ 18 ወራት እንዲኖሩ እንደፈቀደ አስታውቋል፡፡
በአሜሪካ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ኢትዮጵያዊያን ከፈረንጆቹ ሰኔ 2024 እስከ ታህሳስ 2025 ድረስ የሚቆዩበት የመኖሪያ ፈቃድ እንደሚሰጡ ተቋሙ ባወጣው መግለጫ ገልጿል፡፡
የፌደራል መንግሥት ከአንድ ዓመት በፊት የክልል ልዩ ሀይሎችን "መልሼ አደራጃለሁ" የሚል ውሳኔ ማሳለፉን ተከትሎ በአማራ ክልል ግጭት ተከስቷል።
ግጭቱ በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና የፋኖ ታጣቂዎች መካከል የተካሄደ ሲሆን ግጭቱ ተባብሶ መቀጠሉን ተከትሎ በአማራ ክልል ለስድስት ወራት የሚዘልቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል።
ብሪታንያ የኢትዮጵያ አበባ ያለ ግብር ወደ ሀገሯ እንዲገባ ፈቀደች
ሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ የታወጀው ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለተጨማሪ አራት ወራት ተራዝሟል።
የፍትህ ሚንስትር ጌዲዮን ጢሞቲየስ (ዶ/ር) ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት እንዳሉት በአማራ ክልል በታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር በተያያዘ ከ700 በላይ ተጠርጣሪዎች በእስር ላይ እንደሚገኙ መናገራቸው ይታወሳል።
በክልሉ ንጹሀን ዜጎች ኢላማ ተደርገዋል፣ የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላት በመራዊ ከተማ ከ80 በላይ ዜጎችን በጅምላ ገድለዋል የሚል ሪፖርቶች የሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋማት አውጥተዋል፡፡
ከተቋማት ባለፈ አሜሪካ፣ ብሪታንያ፣ የአውሮፓ ህብረት እና ሌሎች ሀገራት በጉዳዩ ዙሪያ ገለልተኛ ምርመራ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የፌደራል መንግስት በበኩሉ መከላከያ ሰራዊት ራሱን ከጥቃት ተከላከለ እንጂ ንጹሃን በጅምላ አልገደለም ጉዳዩም በገለልተኛ አካል አይመረመርም ሲል ምላሽ መስጠቱ አይዘነጋም፡፡