ቻይና ኮሮናቫይረስን ለመቆጣጠር የዉሀን ከተማን በከፊል ዘጋች፡፡
በማእከላዊ ቻይና ሁቤይ ግዛት በምትገኘው ዉሀን ከተማ ከሶስት ሳምንታት በፊትታህሳስ ወር ላይ ምልክቱ የታየው ኮሮናቫይረስ አሁን ላይ በፍጥነት እየተዛመተ ነው፡፡
እስከዛሬ ጥር 14 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ 17 ሰዎች በቫይረሱ ሲሞቱ ሁሉም ሟቾች የዉሀን ከተማ ነዋሪዎች ናቸው፡፡
በቻይና ምልክቱ የታየባቸው ሰዎች ቁጥር በትንሹ 620 መድረሱን ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡ ከቻይና ውጭ በታይላንድ፣ኮሪያ፣ጃፓን፣ዩኤስኤ፣ታይዋን እና ዛሬ ደግሞ በሲንጋፖርም ምልክቱ የታየ ሲሆን አጠቃላይ የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር እየጨመረ በመሄድ ላይ ነው፡፡
የበሽታው ምልክት አስቀድሞ የታየው በውሃን ከተማ የሚገኘው የዱር እና የውሀ ውስጥ እንስሳት ገበያ እንደሆነ ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት፡፡ ለገበያ የሚቀርቡት እንስሳቱ የሀገሬው ሰዎች ለምግብነት የሚጠቀሟቸው ሲሆን የቫይረሱ መነሻም እንስሳቱ ናቸው ተብሏል፡፡ የቫይረሱን መከሰት ተከትሎ ቻይና ገበያውን በአፋጣኝ ዘግታለች፡፡ቫይረሱ በተለያዩ እንስሳት ላይ ቀድሞውንም የተለመደ ነው፡፡
አሁን ደግሞ ቫይረሱ ከሰውነት በሚወጣ ፈሳሽ ንክኪ ከሰው ወደሰው እንደሚተላለፍም ተረጋግጧል፡፡ ለቫይረሱ በፍጥነት መዛመትም ምክኒያቱ ይሄው ነው፡፡
የቫይረሱ መከሰት በሀገሪቱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ በማስከተል ላይ ይገኛል፡፡
ቻይና ከነገ ጀምሮ ለምታከብረው የአዲስ ዓመት በዓል በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የሀገሪቱ ዜጎች ከተለያዩ አካባቢዎች ሊሰባሰቡ ይችላሉ መባሉ ደግሞ ስጋቱን አባብሷል፡፡
ይሄን ስጋት ለመቀነስ በሚል የሀገሪቱን ዋና ከተማ ቤጂንግን ጨምሮ የተለያዩ ከተሞችና ግዛቶች በዓሉ እንዳይከበር ወስነዋል፡፡
በዚህ አስቸጋሪ ወቅት የሚከናወኑ የፊልም ፌስቲቫሎችን ጨምሮ የአምልኮ እና መሰል ህዝብ የሚሰበሰብባቸው ሁነቶች እደሚሰረዙ የሀገሪቱ መንግስት አስታውቋል፡፡
11 ሚሊዮን ህዝብ የሚኖርባት የቫይረሱ መነሻና አብዛኛው ተጠቂዎች የሚገኙባት ዉሀን ከተማ፣ ስርጭቱን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት በከፊልም ቢሆን ተዘግታለች፡፡
ወደ ከተማዋ የሚደረጉ የአውሮፕላንና የባቡር ጉዞዎች እንዲሁም የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎቶች እንዲቋረጡ ተደርገዋል፡፡ በሌላ መንገድ ከከተማዋ የሚወጡ ዜጎችም ቢሆኑ ከመንቀሳቀሳቸው በፊት ምርመራ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ አጠቃላይ ካለው ሁኔታ ጋር ተያይዞ የከተማዋ ድባብ የአለም ፍጻሜ ይመስላል አንድ የዉሀን ከተማ ነዋሪ ለሚዲያዎች እንደተናገረው፡፡
በዉሀን አቅራቢያ የሚገኘው የሁዋንጋንግ ከተማ ባለስልጣናትም በከተማዋ የባቡር እና የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት እንዲቆም አድርገዋል፡፡
ዛሬ በሁለቱም ከተሞች ሲኒማዎች፣ ካፌዎች፣ ቲያትር ቤቶችና የአውደርዕይ ማእከላት ሙሉ በሙሉ ተዘግተዋል፡፡
ቫይረሱ በዚህ ሳምንት በአብዛኛው የቻይና ግዛቶች ተዛምቷል፡፡
ዉሀን ኮሮናቫይረስ የመተንፈሻ አካላትን በማጥቃት ከባድ የሳምባ ምች ያስከትላል፡፡ ከባድ ጉንፋን፣ ሳል፣ ራስ ምታት፣ የጉሮሮ ህመም፣ትኩሳት እና አጠቃላይ የህመም ስሜት የቫይረሱ ምልክቶች ናቸው፡፡
ለዘገባው የተለያዩ ምንጮችን በዋቢነት ተጠቅመናል፡፡