በ2019 በመላው ዓለም በርካታ ባህላዊና ሀይማኖታዊ ፌስቲቫሎች ተከናውነዋል
ፌስቲቫሎች በ2019
ከ80 በላይ ብሔር ብሔረሰቦች ያሏት ኢትዮጰያ በየአመቱ የተለያዩ ሀይማኖታዊና ባህላዊ ፌስቲቫሎችን ታስተናግዳለች፡፡ ከነዚህም በዩኔስኮ የተመዘገቡት የመስቀል ደመራ፣ ጥምቀት፣ የገዳ ስርዓት አካል የሆነው ኢሬቻና የሲዳማ አዲስ ዓመት ፊቼ ጫምባላላ ይገኙበታል፡፡ የተለያዩ የዓለማችን ሀገራትም በርካታ ፌስቲቫሎችን በዓመቱ ያካሂዳሉ፡፡ ከበዚህ ጥቂቱን በዚህ ጽሁፍ እንዳስሳለን፡፡
መስቀል ደመራ
የመስቀል በዓል በኢትዮጵያ ከ1600 ዓመታት በላይ ሃይማታዊና ባህላዊ ትውፊቱን እና ሥርዓቱን እንደጠበቀ የዘለቀ ሲሆን የተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስ የባህል ተቋም (UNESCO) እ.ኤ.አ. በ2013 በዓሉን የዓለም የማይዳሰስ ቅርስ (Intangible Heritage) አድርጎ መዝግቦታል፡፡በዓሉ በየዓመቱ መስከረም 17 የሚከበር ሲሆን የበዓሉ ዋዜማም የተዘጋጀውን ደመራ በመለኮስና በል ልዩ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ክዋኔዎች ይከበራል፡፡ ይህን በዓል ልዩ ከሚያደርጉት ነገሮች አንዱና ዋነኛዉ ከመላዉ ዓለም የሚመጡ ቱሪስቶች የበዓሉ አካል መሆናቸዉ ነው፡፡
ጥምቀት
በየዓመቱ ከጥር 10 እስከ 12 በመላዉ ሀገሪቱ በሚከበረው የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ኃይማኖት ውስጥ እጅግ መንፈሣዊ ክብር የሚሠጣቸው ታቦታት' መስቀሎች' ፅናፅሎች' ዣንጥላዎች' ታላላቅ ድርሣናት' ብርቅና ድንቅ የሆኑ ቅርሶች ወዘተ ይወጣሉ። ካሕናት በአልባሣት ያሸበርቃሉ። ምዕምናን እና ምዕመናት ፀዐዳ ልብሶቻቸውን ይለብሣሉ። ሕፃናት ክርስትና ለመነሣት ይዘጋጃሉ። በዓሉ ዘንድሮም በመላዉ ሀገሪቱ በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ተከብሯል፡፡ በቅርቡም በደቡብ አሜሪካዋ ኮሎምቢያ መዲና ቦጎታ በተደረገው የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች የበይነ መንግሥታት ኮሚቴ ረቡዕ ታኅሣሥ 1, 2012 ዓ.ም. ውሎው ጥምቀትን ጨምሮ አምስት ባህላዊ ቅርሶችን በሰው ልጆች ወካይ ቅርስነት መመዝገቡን በድረ ገጹ አስነብቧል፡፡
የብሔር ብሔረሰቦች ቀን
የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ዘንድሮ ህዳር 29 ቀን 2012 ዓ.ም ለ14ኛ ጊዜ በኦሮሚያ ክልል አዘጋጅነት አዲስ አባባ ላይ ተከብሯል፡፡ በዓሉ በዋናነት የሚከበረዉ የሀገሪቱ መተዳደርያ የሆነው ህገ መንግስት የጸደቀበትና ብሔር ብሔርሰቦች እኩልነታቸው የተከበረበት ዕለትን በማሰብ ነው፡፡ ዘንድሮም “ህገመንግስታዊ ቃልኪዳናችን ለዘላቂ ሰላማችን በሚል መሪ ቃል የተከበረዉ ይህ በዓል ከመላዉ ሀገሪቱ የተዉጣጡ ብሔሮች፤ብሔረሰቦችና ህዝቦች በተገኙበት ተከብሯል፡፡
ኢሬቻ
ኢሬቻ በየዓመቱ ቢሾፍቱ ከተማ ሆረ ሀርሰዴ ላይ ሚሊዮኖች በታደሙበት የሚከበር ሲሆን ዘንድሮ ግን በልዩ ሁኔታ አዲስ አበባ ሊከበር ችሏል፡፡ ይህም ከ150 ዓመት በፊት አዲስ አበባ ልዩ ቦታው ሆረ ፊንፊኔ በመባል ይታወቅ በነበረው ቦታ ላይ የሚከበረውን የኢሬቻ በዓል ለማሰብና ታሪክን ለመዘከር ሲሆን በተመሳሳይ ቢሾፍቱ ሆረ ሀርሰዴ ላይም ተከብሯል፡፡ለበዓሉ ድምቀት ከሰጡት ከዋኔዎች መካከልም ከመላው የሀገሪቱ ክፍሎች በዓሉ ላይ ለመሳተፍ ከሚመጡት የኦሮሞ ተወላጆች በተጨማሪ ሌሎች የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችም የበዓሉ ታዳሚዎች መሆናቸዉ ነዉ፡፡በዚህ መሰረት በዘንድሮ እሬቻ ላይም አላባዎች፤ሲዳማዎች፤ጋሞዎችና ልሎች ብሔረሰቦችም ተሳትፈዉበታል፡፡
ፊቼ ጫምባላላ
«ፊቼ ጫምባላላ»በመባል የሚታወቀው የሲዳማዎች ቀመር በከዋክብት ዑደት ላይ የተመሠረተ ነው። ኢትዮጵያ ብዙ ባህል ያላት ሀገር እንደመሆኗ ከዘመን ቆጠራ አኳያ በየአካባቢው ባሉ ነገሮች፣ ብሔረሰቦች የየራሳቸው መገለጫ የሆኑ ባህላዊ የዘመን አቆጣጠር አላቸው። ከነዚህም መካከል የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በሰው ልጅ ወካይ ቅርስነት የመዘገበው የሲዳማ የዘመን አቆጣጠር ይገኝበታል። የዘንድሮው የፊቼ ጫምባላላ በዓል በተለያዩ ካርኒቫሎችና የጎዳና ላይ ትርኢቶች በሀዋሳ ከተማ ተከብሯል።
ሪኦ ካርኒቫል
በብራዚል ሪኦ ዲ ጄኔይሮ በስፋት የሚከበረዉ የሪኦ ካርኒቫል በየዓመቱ የሚከበር ሲሆን በዓለም ትልቁ ካርኒቫል በመባል ይታወቃል፡፡ዘንድሮም በዓሉ ብራዚል በምትታወቅበት ሳምባ ዳንስ ዉድድሮች ከመጋቢት 1-9 ተከብሯል፡፡በፈረንጆቹ 1723 የተጀመረው የሪኦ ካርኒቫል በየዓመቱ ከ2 ሚልዮን በላይ ሰዎች ይሳተፉበታል፡፡የሪኦ ካርኒቫል በሳምባ ዳንስ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤቶች ውድድር የሚደምቅ ሲሆን አጀማመሩም በአንድ ላይ ተሰባስበው በሚኖሩ ሰዎች መካከል በሚደረግ የሳምባ ዳንስ ውድድር ነበር፡፡
ሶንግክራን
ሶንግክራን በታይላንድ በዉሃ ፌስቲቫል የሚከበር ካርኒቫል ነው፡፡ ሰንግክራን የታይላንድ አዲስ ዓመት ሲሆን በደቡብና ደቡብ ምስራቅ ኤዥያ ሀገራት በስፋት ይከበራል፡፡በዓሉ በፈረንጆቹ አቆጣጠር በየዓመቱ ከሚያዝያ 13 እስከ ሚያዝያ 15 ሊከበር ይችላል፡፡የ2019 ሰንግክራን ፌስትቫልም በታይላንድ ትልቁና ታዋቂ በሆነው የዉሃ ፌስቲቫል ደምቆ ተከብሯል፡፡የበዓሉ ተሳታፊዎችም የዉሃ ሽጉጥ፤የዉሃ ቱቦና ልሎች ቁሳቁሶችን በማዘጋጀት ዉሃ ዉስጥ በመግባትና በመዘፈቅ በተዝናኖት ያከብሩታል፡፡