ጣሊያን ኤምባሲ የሚገኙት ሁለቱ የደርግ ከፍተኛ ባለሥልጣናት እንዲለቀቁ ተወሰነ
ግለሰቦቹ ላለፉት 30 ዓመታት በኢትዮጵያ የጣሊያን ኤምባሲ ተጠልለው ይገኛሉ

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዛሬ በዋለው ችሎት ሁለቱ ግለሰቦች በአመክሮ እንዲፈቱ ወስኗል
ላለፉት 30 ዓመታት በኢትዮጵያ የጣሊያን ኤምባሲ ተጠልለው የሚገኙት ሁለቱ የደርግ ከፍተኛ ባለስልጣናት ሌተናል ኮሎኔል ብርሃኑ ባየህና ሌተናል ጄነራል አዲስ ተድላ እንዲለቀቁ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወሰነ፡፡ ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን የሰጠው የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በባለሥልጣናቱ ላይ ተላልፎ የነበረው የሞት ፍርድ ወደ እድሜ ልክ እስራት እንዲቀየር መሻሻሉን ከአራት ቀናት በፊት ይፋ ማድረጋቸውን ተከትሎ ነው፡፡
ፍርድ ቤቱ ዛሬ በዋለው ችሎት የሁለቱን ግለሰቦች ጉዳይ ተመልክቶ በአመክሮ እንዲፈቱ ውሳኔ ማሳለፉን የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዘግቧል። ሁለቱም ቀደም ብሎ በእነ ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም የክስ መዝገብ ስር የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው የነበረ ሲሆን ፣ የአዲስ አበባ ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር የአመክሮ አስተያየትን ከይቅርታ ሰነዶች ጋር ለፍርቤት ማቅረቡን አስታውቋል።
የአዲስ አበባ ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር “የዕድሜ ልክ ፍርደኛ በአመክሮ መታሰር ያለበት ለ20 አመት በመሆኑ ግለሰቦቹ በአመክሮ ቢፈቱ ተቃውሞ የለንም” የሚል አቤቱታ ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል።
ፍርድ ቤቱም ለጉዳዩ አግባብነት ያላቸውን የሕገ መንግሥት ድንጋጌዎችና ሌሎች ሕጎች መርምሮ ግለሰቦቹ ከኤምባሲው እንዲለቀቁ ወስኖ ለፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግና ለፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ትዕዛዝ ሰጥቷል። ትዛዙም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ለጣሊያን ኤምባሲ እንዲሁም ለሁለቱ የቀድሞ ፍርደኞች እንዲደርስ አዟል።