አውሮፕላኑ ከጁባ ወደ ሰሜናዊ ባህር ኤል ጋዛል ክልል ዋና ከተማ አዊል ሲበር ነበር ተብሏል
በጁባ በደረሰው የአውሮፕላን አደጋ የበርካታ ሰዎች ህይወት አልፏል
ከደቡብ ሱዳን ጁባ ተነስቶ ሲበር የነበረ የጭነት አውሮፕላን በመከስከሱ ምክንያት የበርካታ ሰዎች ህይወት ማለፉን የተለያዩ የሃገሪቱ ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡
ዘገባውን ቀድሞ ያወጣው አይ ራዲዮ ጣቢያ አውሮፕላኑ ሳውዝ ዌስት የተሰኘ አየር መንገድ ንብረት ነው ብሏል፡፡
የሟቾቹ ቁጥር ለጊዜው አለመታወቁንም ነው የዘገበው፡፡
በአደጋው የበርካታ ሰዎች ህይወት ማለፉን የአይን እማኞች አረጋግጠውልኛል ያለው ኒያማይል የተሰኘ ሚዲያ በበኩሉ አውሮፕላኑ ወደ ሰሜናዊ ባህር ኤል ጋዛል ክልል ዋና ከተማ አዊል ለመብረር ከጁባ ከተነሳ ጥቂት ደቂቃዎች በኋላ መከስከሱን ዘግቧል፡፡
“ ዛሬ ጠዋት በጁባ የአውሮፕላን መከስከስ አደጋ አጋጥሟል፡፡ አውሮፕላኑ የሳውዝ ዌስት አየር መንገድ ነው፡፡ አየርመንገዱ አሮጌ አውሮፕላኖችን እንደሚጠቀም ታውቃለህ ለዚህም ነው አደጋው የደረሰው፡፡ ትክክለኛው ቁጥር ባይታወቅም እንኳን በርካታ ሰዎች ሞተዋል” ሲሉም ነው አንድ በስፍራ የነበሩ የዓይን እማኝ ለኒያማይል የተናገሩት፡፡
አንድ ሰው ብቻ መትረፉንም ገልጸዋል፡፡
የአደጋውን መንስዔ በተመለከተ ግን እስካሁን በውል የታወቀ ነገር የለም፡፡