ከ19 ሞቶች መካከል ከአንድ በላይ የሚሆነው ከብክለት የተነሳ የሚያጋጥም ነው
በብሪታኒያ ከመኪና አደጋ ይልቅ በአየር ብክለት የሚሞቱት ያይላሉ
ዴይሊ ሜይል በከተማ ከሚኖሩ ብሪታኒያውያን አንድ አምስተኛው ከአየር ብክለት ጋር በተያያዘ ይሞታሉ በሚል አንድን ሪፖርት ዋቢ አድርጎ ዘግቧል፡፡ ከ19 ሞቶች መካከል ከአንድ በላይ የሚሆነው ከብክለት የተነሳ የሚያጋጥም ነው ብሏል፡፡ ከተማ ኗሪ ብሪታኒያውያን ከመኪና አደጋ በ25 በመቶ በበለጠ በአየር ንብረት እንደሚሞቱም ነው ዘገባው የሚያትተው፡፡
ከፍ ያለ የገዳይነት ደረጃ ያላቸው ብናኞች፣አቧራ እና ጥቀርሻ መሰል በካይ ነገሮች በደቡባዊ ብሪታኒያ በዝተው እንደሚስተዋሉም የከተሞች ተራድዖ ድርጅት ሪፖርት አመልክቷል፡፡
ሎንደን፣ ሱቶን እና ስላፍ የብክለቱ ቀዳሚ ሰለባ ናቸው፡፡በከተሞቹ ከሚያጋጥሙ 19 ሞቶች መካከልም ከአንድ በላይ የሚሆነው ከብክለት የተነሳ የሚፈጠር ነው፡፡
የስኮትላንዷ አበርዲን ዝቅተኛ የብክለት መጠንና ከሌሎቹ የተሻለ ተጋላጭነት አላት፡፡ በከተማዋ ከሚያጋጥሙ 33 ሞቶች መካከልም አንዱ በብክለት የሚፈጠር ቢሆን ነው፡፡
ዱንዴ፣ግላስጎው፣ብላክፑል እና ኤደንበርግም እንደ አበርዲን ሁሉ ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው፡፡
በመርዛማ አየር መተንፈስ እጅግ እንደሚከብድና ለማንም ጎጂ እንደሆነ የተናገሩት የብሪቲሽ ለንግ ፋውንዴሽኑ ዛክ ቦንድ ሳንባ፣ደም ወደ ጭንቅላት መፍሰስንና ካንሰርን ጨምሮ ለዘርፈ ብዙ የጤና መጓደሎች ሊዳርግ እንደሚችል አሳስበዋል፡፡
የከተሞች ተራድዖ ድርጅትም የሃገሪቱ መንግስት ልክ እንደ የዓለም የጤና ድርጅት ሁሉ ጥብቅ የቁጥጥር ህግጋትን ሊያወጣ እንደሚገባ አሳስቧል፡፡