የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ም/ቤት የኢኮኖሚ ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አብዱላሂ ሶጃር በታጠቁ ኃይሎች ተገደሉ
ለመንግስት ሥራ ጉዳይ ከአሶሳ ወደ ነቀምት በመጓዝ ላይ የነበሩት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት የኢኮኖሚ ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አብዱላሂ ሶጃር በታጠቁ ኃይሎች ተገደሉ፡፡
የክልሉ ምክር ቤት የኢኮኖሚ ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የነበሩት አቶ አብዱላሂ ሶጃር ዛሬ ጠዋት ከአሶሳ ወደ ነቀምት በመጓዝ ላይ እያሉ የዳቡስ ወንዝን ተሻግሮ በኦሮሚያ ክልል ቤንጓ አካባቢ በታጣቂዎች መገደላቸውን የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መለሠ በየነ ተናግረዋል፡፡
በጥቃቱም በመኪናው ውሰጥ የነበሩ 1 ወንድ እና 1 ሴት ላይ ጉዳት ደርሶባቸው በህክምና እርዳታ ላይ እንደሚገኙም አቶ መለሠ ጠቅሰዋል፡፡
ከክልሉ ተነስቶ አሮሚያ ክልልን የሚያቋርጠው መንገድ ባለፉት ዓመታት ከፍተኛ ስጋት የነበረበት በመሆኑ የትራንስፖርት አገልግሎት ተቋርጦ የቆየ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ሁለቱ ክልሎች እያከናወኗቸው ባሉ የጋራ የሠላምና የልማት ሥራዎች አንጻራዊ ሠላም ተፈጥሮ እንደነበርም አቶ መለሠ ገልጸዋል፡፡
"ክስተቱ የሁለቱን ክልል ህዝቦች አይወክልም" ያሉት አቶ መለሠ፣ "የቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና የኦሮሚያ ክልሎች የጀመሩት የጋራ የሠላምና የልማት ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል"ብለዋል፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የመረጃው ምንጭ ነው፡፡