ቦሪስ ጆንሰን የተገደሉት የኢራን ጄነራል ለብዙዎች መሞት እጃቸው አለበት አሉ
የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ሰሞነኛውን የኢራን ጉዳይ ተከትሎ ሚኒስትሮቻቸውን ለስብሰባ መጥራታቸውን ዴይሊሜይል ዘግቧል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢራን የብሪታኒያ ወታደሮች ላይ ግዲያ እፈጽማለሁ ካለች በኋላ ነው ለስብሰባ የጠሯቸው፡፡
ከሰሞኑ ከኢራኑ ጄነራል ግድያ ጋር በተያያዘ ዓለም ውጥረት ውስጥ የገባ ሲሆን ይህንኑ ስጋት የተመለከተ ውይይት ለማድርግ ነው የታሰበው ተብሏል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ጆንሰን ከሰሞኑ የተገደሉት የኢራን ጄነራል ለበርካቶች ሞት ምክንያት እንደነበሩም ተናግረዋል፡፡
ከግድያው በኋም በአካባው ያለው ውጥረት እንዲረግብ ቦሪስ ጆንሰን ጠይቀዋል፡፡
ከክስተቱ በኋላ ቦሪስ ጆንሰን ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕና ከአውሮፓ ሀገራት መሪዎች ማለትም ከጀርመኗ መራሄተ መንግስት አንጌላ ሜርኬልና ከፈረንሳዩ ፕሬዘዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር መወያየታቸውን አስታውቀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጄነራሉ መገደል ብሪታኒያ አታዝንም፤ ሀዘንም አትቀመጥም ያሉ ሲሆን ሟቹ ወታደራዊ ሃላፊ በሺዎች ለሚቆጠሩ ንጹሃን ሞት ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል ብለዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም ጄነራል ሱሊማኒ ከብሔራዊ ጥቅማችን በተቃራኒ የቆሙ ሰው ነበሩ ሲሉ ነው ጆንሰን የተደመጡት፡፡
ያም ሆነ ይህ አሁን ላይ በቀጣናው ያለው ውጥረቱ እንዲረግብ መደረግ አለበትም ብለዋል፡፡
ኢራን ከከፍተኛ ወታደራዊ አዛዧ መገደል በኋላ የአጸፋ እርምጃ እንደምትወሰድ ማስታወቋ የሚታወስ ሲሆን ከዚህ ውስጥ የብሪታኒያ ወታደሮችም ኢላማ ሊሆኑ ይችላሉ መባሉን ተከትሎ ነው የብሪታኒያ ቁልፍ የካቢኔ አባላት ለስብሰባ የተቀመጡት፡፡
አሜሪካ የተገደሉት ጄነራል ኢራን በመካከለኛው ምስራቅ የተልዕኮ ጦርነት እንድታደርግና በመቶዎች የሚቆጠሩ አሜሪካውያን መንገድ ላይ በተጠመዱ ቦምቦች እንዲሞቱ ያደረጉ መሆናቸውን መግለጿ ይታወሳል፡፡