የፕሪሚየር ሊጉ የመጀመሪያ ሳምንት ተጠባቂ ጨዋታ፤ ቼልሲ ከሊቨርፑል
አዲሱ የቼልሲ አሰልጣኝ ማውሪሲዮ ፖቼቲኖ በስታንፎርድ ብሪጅ ቀያዮቹን በመግጠም ስራቸውን ይጀምራሉ
ቼልሲና ሊቨርፑል ባለፉት ስድስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል
የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ የመጀመሪያውን ሳምንት ተጠባቂ ጨዋታ ያስተናግዳል።
የምዕራብ ለንደኑ ክለብ ቼልሲ በስታንፎርድ ብሪጅ የየርገን ክሎፑን ሊቨርፑል ይገጥማል።
በርካታ ተጫዋቾቹን በክረምቱ የዝውውር መስኮት የሸጠው ቼልሲ ከሪያል ማድሪድ በውሰት ያስፈረመውን ግብ ጠባቂ ኬፓ አዚራባላጋ በዛሬው ፍልሚያ ይጠቀማል ተብሏል።
የቼልሲ አዲሱ አሰልጣኝ ማውሪሲዮ ፖቼቲኖ የስታንፎርድ ብሪጁን ፍልሚያ በማሸነፍ የድል ጉዟቸውን እንደሚጀምሩም ተስፋ አድርገዋል።
አሃዞች የሚያሳዩት ግን የሰማያዊዮቹ እና ቀያዮቹ ፍልሚያ በአቻ ውጤት ሲደመደሙ ነው።
ሁለቱ ቡድኖች በተገናኙባቸው ስድስት ጨዋታዎች በአቻ (አራቱ ያለምንም ጎል) መጠናቀቃቸውንም ጎል ስፖርት አውስቷል።
ቼልሲ በፕሪሚየር ሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታ ሊቨርፑልን በሜዳው ለመጨረሻ ጊዜ ያስተናገደው በ1937 ሲሆን፥ ሰማያዊዮቹ 6 ለ 1 በሆነ ውጤት አሸንፈው ነበር።
ቦርሲያ ዶርትሙንድን በመጋቢት ወር 2023 በሻምፒዮንስ ሊጉ ካሸነፉ በኋላ በየትኛውም ውድድር ድል ማድረግ የተሳናቸው ቼልሲዎች ባለፈው የውድድር አመት በ38 ነጥብ 12ኛ ደረጃን ይዘው ማጠናቀቃቸውም አይዘነጋም።
ዛሬ በስታንፎርድ ብሪጅ ለሚያስተናግዱት ሊቨርፑል የማይበገሩት ሰማያዊዮቹ ዘንድሮስ የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፏቸውን ያረጋግጣሉ ወይ የሚለው አጠያያቂ ነው።
የየርገን ክሎፑ ሊቨርፑል በፕሪሚየር ሊግ የመክፈቻ ጨዋታዎች ያለመሸነፍ የ10 አመት ጉዞውስ ዛሬ ይፈተን ይሆን? ምሽት 12 ከ30 ጀምሮ በሚካሄደው ጨዋታ ምላሽ ያገኛል።