ቻይና በቀጣይ ሳምንት በታይዋን አካባቢ ወታደራዊ ልምምድ ለማድረግ ተዘጋጅታለች
የታይዋን ምክትል ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሌይ በአሜሪካ ጉብኝት እያደረጉ ነው።
ምክትል ፕሬዝዳንቱ በኒውዮርክ እና ሳንፍራንሲስኮ ያደረጉት ጉብኝት ቻይናን አስቆጥቷል።
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ የዊሊያም ሌይ ጉብኝት የሀገሪቱን ሉአላዊነት የተዳፈረ ነው ብሏል።
ሌይ ታይፒን ከቤጂንግ የመገንጠል እሳቤን የሚያቀነቅኑ እና “ሁሌም ችግር ፈጣሪ” ሲልም ገልጿቸዋል።
በታይዋን በቀጣይ በሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ዋነኛው እጩ ተፎካካሪ ዊሊያም ሌይ በቻይና ከዚህ ቀደምም ተደጋጋሚ ትችት ይሰነዘርባቸዋል።
በምርጫ ቅስቀሳቸውም ለታይዋን ነጻነት እንደሚሰሩ ሲናገሩ መደመጣቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።
ምክትል ፕሬዝዳንቱ ወደ ፓራጓይ ሲያመሩ ሁለት ጊዜ በአሜሪካ የማረፋቸውን ጉዳይ በቀላሉ አንመለከተውም ያለው መግለጫው፥ ሌይ ከአሜሪካ ባለስልጣናት ጋር ምን እንደተነጋገሩ እየተከታተልን ነው ብሏል።
ቻይና እንደ አንድ ሉአላዊ ግዛቷ የምትመለከታት ታይዋን ከቅርብ አመታት ወዲህ ከአሜሪካ ጋር ጥብቅ ወዳጅነት መስርታለች።
ከዋሽንግተን በቢሊየን ዶላር የምትሸምተው የጦር መሳሪያ እያደገ መሄድና የቤጂንግ ጦር ልምምድ የታይዋን ሰርጥን ውጥረት እያባባሰው ይገኛል።
ቻይና የምክትል ፕሬዝዳንቱን የአሜሪካ ጉብኝት ምክንያት በማድረግም በቀጣዩ ሳምንት በታይዋን አቅራቢያ ወታደራዊ ልምምድ ታደርጋለች ተብሏል።
ቤጂንግ ባለፈው ሚያዚያ ወርም የታይዋን ፕሬዝዳንት ሳይ ኢንግ ዌን ከአሜሪካ ኮንግረንስ አፈጉባኤ ኬቪን ማካርቲ ጋር በተወያዩ ማግስት ግዙፍ ወታደራዊ ልምምድ ማድረጓ ይታወሳል።