እ.ኤ.አ. በ2019 በአውሮፕላን መከስከስ የሞቱ ሰዎች ቁጥር በግማሽ ቀነሰ
“ቱ 70” የተባለው የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ዘርፍ አማካሪ ድርጅት አደረግሁት ባለው ጥናት መሰረት እ.ኤ.አ. በ2019 በአውሮፕላን መከስከስ አደጋ ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት (2018) ጋር ሲነፃፀር የ50 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱን አስታውቋል፡፡
እ.ኤ.አ. በ2018 ባጋጠሙ አደጋዎች የ534 ተሳፋሪዎች ህይወት ማለፉ ተመዝግቦ ነበር ያለው ተቋሙ በተጠናቀቀው 2019 ደግሞ የ257 ሰዎች ህይወት ማለፉን አስታውቋል፡፡ ይህም ቀደም ካለው ዓመት የ50 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል ብሏል ጥናቱ፡፡
ሆኖምግን ጥናቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቦይንግ ማክስ 737 አውሮፕላን ምክንያት የደረሰበትን እና የበርካቶች ህይወት ያለፈበትን አደጋ አላካተተም፡፡
የአቪዬሽን ኢንዱስትሪው ከዓመት ዓመት እያደገ ነው በሚባልበት በዚህ ወቅት ነው አደጋዎች ቀንሰዋል እየተባለ የሚገኘው፡፡
በ2019 በአጠቃላይ ግዙፍ አየር መንገዶችን የፈተኑ 86 አደጋዎች አጋጥመዋል፡፡ ከነዚህ ውስጥ 8ቱ የ257 ተጓዦችን ህይወት ነጥቀዋል፡፡
ግዙፍ የመንገደኞች የአውሮፕላኖች ከሚያደርጓቸው 5 ነጥብ 58 ሚሊዬን በረራዎች መካከልም አንድ የሞት አደጋ ያጋጥማል ይላል ሪፖርቱ፡፡
2019 በመንገደኞች አቪዬሽን ዘርፍ አንጻራዊ ሰላም የተስተዋለበት ነበር የሚለውና አደጋዎችን እየተከታተለ የሚመዘግበው አቪዬሽን ሴፍቲ ኔትዎርክ በ2018 ካጋጠሙ 160 አደጋዎች መካከል 13ቱ እጅግ አስከፊ እንደነበሩና የ534 ተሳፋሪዎችን ህይወት እንደነጠቁ አስቀምጧል፡፡
በዘርፉ ሰላማዊ ሆኖ የሚጠቀሰው ዓመት እ.ኤ.አ. 2017 ነው፡፡ በዓመቱ 13 አደጋዎች ቢያጋጥሙም 2ቱ ብቻ ናቸው የከፉ ሆነው የ13 ሰዎችን ህይወት የነጠቁት፡፡