የፍሎይድ ገዳይ ፖሊስ ዴሬክ ቼቪን በቀጣዩ ሰኞ ዕለት ፍርድ ቤት ይቀርባል ተብሏል
የሰዓት እላፊ ድንጋጌውን በመጣስ በአሜሪካ የሚደረጉ ሰልፎች ተባብሰው ቀጥለዋል
ባለፈው ሰኞ ጆርጅ ፍሎይድ የተባለ ጥቁር አሜሪካዊ በሚኒያፖሊስ ከተማ በፖሊስ በግፍ መገደሉን በመቃወም የተፈጠረውን አለመረጋጋት ለማስቆም በብዙ የአሜሪካ ከተሞች የሰዓት እላፊ ታውጇል፡፡
ይሁንና በሀገሪቱ በርካታ አካባቢዎች የሰዓት እላፊውን ችላ በማለት የሚካሄዲ የተቃውሞ ሰልፎች ተባብሰው የቀጠሉ ሲሆን፣ ሱቆች ተዘርፈዋል ፣ መኪኖች ተቃጥለዋል ፣ ሕንፃዎች ጥቃት ተሰንዝሮባቸዋል፡፡ አድማ በታኝ ፖሊሶች አስለቃሽ ጭስ እና የጎማ ጥይት በመጠቀም ሰልፎቹን ለመበተን ሚያደርጉትን ትግል ቀጥለዋል፡፡
ልዩ ሃይል ፖሊሶችበሚኒያፖሊስ
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ “በጆርጅ ፍሎይድ ሞት ባዝንም ዓመፅ እንዲነግስ ግን አልፈቅድም” ብለዋል፡፡
የ 44 ዓመቱ ዴሬክ ቼቪን የተሰኘ ነጭ የቀድሞ የፖሊስ መኮንን በሚኒሶታ የ 46 ዓመቱን ፍሎይድድ በመግደል ወንጀል ክስ ተመስርቶበታል፡፡ ቼቪን ባለፈው ሰኞ ዕለት ከ8 ደቂቃ በላይ የፍሎይድን አንገት በጉልበቱ ከአስፓልት ጋር አጣብቆ በመቆየት ለህልፈት እንደዳረገው በስፍራው በነበረ ግለሰብ የተቀረጸ ቪዲዮ ያሳያል፡፡ ጆርጅ ፍሎይድ በተደጋጋሚ መተንፈስ እንዳልቻለ በመግለጽ እንዳይገድለው ሲማጸንም በቪዲዮው ተስተውሏል፡፡
ዴሬክ ቼቪን በቀጣዩ ሰኞ ዕለት ፍርድ ቤት እንደሚቀርብም የሲኤንኤን ዘገባ ያሳያል፡፡ ይሁን እንጂ ግድያው በተፈጸመበት ወቅት ከእርሱ ጋር የነበሩ ሌሎች ሶስት ፖሊሶችም እንዲከሰሱ ሰልፈኞቹ በመጠየቅ ላይ ናቸው፡፡ ሶስቱ ፖሊሶች ከዴሬክ ቼቪን ጋር ከስራ መሰናበታቸው ይታወቃል፡፡
ቢያንስ በ30 የአሜሪካ ከተሞች ድርጊቱን የሚያወግዙ ሰልፎች ተካሂደዋል ፤ በመካሄድም ላይ ናቸው፡፡ ሰልፎቹ በአብዛኛው ሰላማዊ ቢሆኑም አልፎ አልፎ ሀይል የተቀላቀለባቸው እርምጃዎች እየተወሰዱ ነው፡፡
ህዝባዊዉን አመጽ ለማብረድ በአንድ አንድ ከተሞች የሀገሪቱ ልዩ ብሔራዊ ሀይል ተሰማርቷል፡፡ በሎሳንጀለስ ደግሞ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል፡፡
እስካሁን ከተቃውሞ ሰልፎቹ ጋር ተያይዞ 2 ሰዎች (1 የፖሊስ አባል እና አንድ የሰልፉ ተሳታዊ) ህይወታቸው አልፏል፤ በሚኒያፖሊስ የሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ተቃጥሏል፤ በሚስሪ የሚገኘው ፈርጉሰን ፖሊስ ጣቢያ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል ፣ በኒውዮርክ 20 የፖሊስ መኪኖች ተቃጥለዋል ፤ በተለያዩ ከተሞች በርካታ የቢዝነስ ተቋማት ተዘርፈዋል ቃጠሎ እና ጉዳትም ደርሶባቸዋል፡፡
በሎሳንጀለስ ፖሊስ ዲፓርትመንት የሚገኝ ሱቅ በቃጠሎ ላይ
ተቃውሞውን ተከትሎ በትዊተር ገጻቸው ካሰፈሯቸው ጽሁፎች አንዱ አመጽን የሚያባብስ ነው በሚል በኩባንያው የተወገደባቸው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ትናንትና ለዘብተኛ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ “የፍሎይድ መገደል የአሜሪካውያንን ቁጣ ቀስቅሷል” ያሉት ትራምፕ “ሰላምን ከሚፈልጉ አሜሪካውያን ጋር በትብብር እቆማለሁ” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ህገወጥ ድርጊቶች ሊቆሙ እንደሚገባ ያሳሰቡት ፕሬዝዳንቱ “አመጽ እንዲነግስ አልፈቅድም” ብለዋል፡፡
በሚኔሶታ በጎ ፈቃደኞች ለሰልፈኞች ምግብና መጠጥ እያሰናዱ
የዲሞክራቶች እጩ በመሆን በቀጣዩ ምርጫ ከትራምፕ ጋር ለፕሬዝዳንትነት የሚወዳደሩት ጆ ባይደን ህዝቡ ቁጣውን መግለጹን በማድነቅ መግለጫ በሰጡበት ወቅት ከተቃውሞው ጋር ተያይዞ የሚደረጉ ዝርፊያዎች እና ንብረቶችን የማውደም ተግባራት ግን እንዲቆሙ ጠይቀዋል፡፡