ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የስልጣን ዘመናቸውን ሳይጨርሱ ከስልጣን ይነሱ ይሆን?
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከስልጣን እንዲነሱ በአሜሪካ ኮንግረስ የተከሰሱ (ኢምፒችመንት የተካሄደባቸው) በታሪክ ሶስተኛው ፕሬዝዳንት ሆነዋል፡፡
ኮንግረሱ በፕሬዝዳንቱ ሁለት ክሶች ላይ ትናንት ታህሳስ 08 ቀን 2012 ዓ.ም. ለ12 ሰዓታት ያክል የዘለቀ ክርክር ካደረገ በኋላ ነው በፕሬዝዳንቱ ቀጣይ እጣ ፋንታ ዙሪያ ድምጽ የሰጠው፡፡
የፕሬዝዳንቱ ክሶች ምንድናቸው?
በሀገሪቱ የታችኛው የህዝብ ተወካዮጭ ም/ቤት (በኮንግረሱ) አፈ ጉባኤ ናንሲ ፕሎሲ አነሳሽነት ከቀረቡትየፕሬዝዳንቱ ሁለት ክሶች የመጀመሪያው ፕሬዝዳንቱ ስልጣናቸውን ያለአግባብ ተጠቅመዋል የሚል ነው፡፡ የዚህኛው ክሳቸው ጉዳይ ደግሞ ከሀገረ ዩክሬይን ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ ይሄውም ከዩክሬይኑ አዲስ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለኒስኪ ጋር በስልክ ባደረጉት ንግግር ፕሬዝዳንቱ ሁለት ውለታዎችን እንዲውሉላቸው እና ለዚህም በእጅ መንሻነት ወታደራዊ ድጋፍ ለመስጠት ትራምፕ ቃል ገብተዋል የሚል ነው፡፡
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከዩክሬይኑ አቻቸው የፈለጉት የመጀመሪያው ውለታ የቀድሞው ተቀናቃኛቸው እና ምክትል ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ልጃቸው በቦርድ አባልነት ካገለገለው ከዩክሬይኑ የተፈጥሮ ጋዝ ኩባኒያ ቡሪስማ ጋር ያላቸው ግንኙነት የተዛባ እንደሆነ የሚያረጋግጥ ጥናት እንዲያስደርጉ የሚጠይቅ ሲሆን ሁለተኛውና ከዚሁ ጋር ተያያዥነት ያለው ደግሞ በ2016ቱ ምርጫ ጣልቃ የገባችው ሩሲያ ሳትሆን በኩባንያው ተጽእኖ ዩክሬይን እንደሆነች የሚያመላክት የሴራ ምርመራ እንዲካሄድ ነው፡፡
ፕሬዝዳንቱ የቀረበባቸው ሁለተኛ ክስ ደግሞ ኮንግረሱ በእሳቸው ላይ ምርመራ እንዳያደርግ ግብረአበሮቻቸውን ከጎናቸው በማሰለፍ በኮንግሰሱ ስራ ላይ ጣልቃ ገብተዋል የሚል ነው፡፡
የኮንግረሱ ውሳኔ
በሁለቱ ክሶች ላይ ዲሞክራቶቹ የቁጥር ብልጫ ባለቸው በኮንግረሱ አባላትለ12 ሰዓታት የቆየ ዘለግ ያለ ክርክር የተደረገ ሲሆን በስተመጨረሻም ዲሞክራቶቹ ክሱን በመደገፍ ሪፓብሊካኖቹ ደግሞ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በመቃወም በየጎራቸው ድምጽ ሰጥተዋል፡፡
የመጀመሪያው ክስ 230 ለ 197 በሆነ ድምጽ ሲጸድቅ ሁለተኛው ደግሞ 229 ለ 198 በሆነ ድምጽ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ በዚህም ፕሬዝዳንቱ ከስልጣን እንዲወርዱ ኮንግረሱ በአብላጫ ድምጽ ውሳኔውን አሳልፎ የመጨረሻ ውሳኔ እንዲሰጥበት ጉዳዩን ለላይኛውምክር ቤት ለሴኔቱ መርቷል፡፡ በኮንግረሱ የውሳኔ ሂደት ወቅት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ክሳቸውን የአክራሪ ግራ ዘመሞች የወረደ ውሸት እና በሪፓብሊካን ላይ የተሰነዘረ ጥቃት ሲሉ በተደጋጋሚ በተዊተር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡
ንጽህናቸውን በሚጠቁም መልኩ እኔ ከተከሰስኩ ቀጣይ የዐሜሪካ ፕሬዝዳንቶች ሁሉ ይከሰሳሉም ቢለው ጽፈዋል፡፡
ወደስልጣን ከመምጣታቸው በፊት ጀምሮ በአወዛጋቢነታቸው የቀጠሉት የእድሜም የገንዘብም ባለጸጋው ፐሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ ከስልጣን እንዲወርዱ ተከሰው በኮንገረሱ ውሳኔ የተላለፈባቸው የልእለ ሃያሏ ሀገር ሶስተኛ መሪ ናቸው፡፡ ከዚህ ቀደም የእሳቸው እጣ የደረሳቸው 17ኛው ፕሬዝዳንት አንድሪው ጆንሰን እና 42ኛው ፕሬዝዳንት ቢል ክሊንተን ናቸው፡፡
ምንም እንኳን በዚህ ሂደት ከስልጣን የወረደ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባይኖርም፣ በዚህ ልክ ተከሶ ለቅሌት መዳረግ ግን የትኛውም ፕሬዝዳንት የማይፈልገው አሳፋሪ ድርጊት ነው፡፡
ቀጣይ የሴኔቱ ውሳኔ ምን ሊሆን ይችላል?
በቀጣይነት ሴኔቱ የሚያሳልፈው ውሳኔ የትራምፕን እጣ ፋንታ የሚወስን ቢሆንም ሪፓብሊካኖቹ ከሚበዙበት ምክር ቤት ግን ፕሬዝዳንቱን የሚያስከፋ ውሳኔ ይተላለፋል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ የነጩ ቤተመንግስትም ፕሬዝዳንቱ በሴኔቱ ሙሉ እምነት እንዳላቸው፣ የኮንግረሱን ውሳኔ ተከትሎ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
53 ሪፓብሊካኖችን እና 45 ዲሞክራቶችን በአባልነት የያዘው ሴኔቱ በሁለት ሶስተኛ ድምጽ ካጸደቀ ነው ፕሬዝዳንቱ ከኃላፊነታቸው ሊነሱ የሚችሉት፡፡
ሴኔቱ በክሱ ላይ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ መክሮ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል፡፡ ባልተጠበቀ መልኩ የሴኔቱ ውሳኔ ፕሬዝዳንቱን ከስልጣን የሚያሰናብት ከሆነ ደግሞ ምክትላቸው ማይክ ፔንስ በትራምፕ ዙፋን ላይ ተቀምጠው እስከ አውሮፓውያኑ ጥር 20 ቀን 2021 ዓ.ም. ቀሪውን ጊዜ የታላቋ ሀገር መሪ ይሆናሉ፡፡