በርካታ የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት የኢንተርኔት መቆራረጥ እንዳጋጠማቸው ተገለጸ
ኬንያ፣ ሱማሊያ፣ ኡጋንዳ፣ ታንዛኒያናና ሩዋንዳ የኢንርኔት መቆራረጥ ካጋጠማቸው ሀገራት መካል ናቸው
በምስራቅ አፍሪካ የሚገኙ አገልግሎት አቅራዎች ችግር መኖሩን አምነዋል
በበርካታ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ከትናንት ምሽት አንስቶ ከፍተኛ የሆነ የኢንተርኔት መቆራረጥ ችግር እንዳጋጠማቸው ተገለጸ።
የኢንተርኔት አገልግሎት መቆራረጥ ካጋጠማቸው የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት መካከልም ኬንያ፣ ሱማሊያ፣ ኡጋንዳ፣ ታንዛኒያና ሩዋንዳ ይገኙበታል የተባለ ሲሆን፤ ተጠቃሚዎች ከኢንተርኔት አገለግሎት መቆራረጥና መንቀራፈፍ ጋር ተያይዞ ሲያማርሩም ተሰምተዋል።
የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የኢንተርኔት አገልግሎት የተቋረጠው ውቅያኖስ ውስጥ የተዘረጉ የኢንተርኔት መስመሮች ባልታወቀ ምክንያት በመቆረጣቸው እንደሆነ ተነግሯል።
የኢንተርኔት ግኑኝነትን የሚከታተለው ክላውድፍላር ራዳር እንዳለው በኢንተርኔት መቆራረጡ በክፉኛ ከተጠቁ ሀገራ መካከል ታንዛኒያ ቀዳሚዋ ስትሆን፤ የሀገሪቱ የኢንተርኔትየትራፊክ ፍሰት ከሚጠበቀው ደረጃ በ30 በመቶ ዝቅ ብሏል።
የታንዛኒያ ሲቲዝን ጋዜጣ “የተከሰተው የኢንተርኔት መቆራረጥ ዋና ዋና የኔትወርክ ቻናሎችን የጎዳ ነው” ሲል ገልጿል።
በርካታ ኬንያውያንም የኢንተርኔት መቆራረጡ እንዳማረራቸው ሲገልጹ ተሰምተዋል፤ ኤርቴል እና ሳፋሪኮም የተባሉ የኬንያ የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢ ድርጅቶችም የኢንተርኔት መቆራረጥ ችግሩ መከሰቱን ገልጸው፤ ለማስተካከል እየሰሩ መሆኑን ለደንበኞቻው አስታውቀዋል።
የኡጋንዳው የቴሌኮም አቅራቢ ድርጅት ኤርቴል ኡጋዳ የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡን እንደሚያውቅ የገለጸ ሲሆን፤ የሩዋንዳው ኤምቲኤን “የአለም አቀፍ የኢንተርኔት ግንኙነት መስመር ላይ ብልሽት ማጋጠሙን ገልጿል።
በማላዊ፣ ሞዛምቢክ እና ማዳካስካርም የኢንተርኔት አገልግሎት መቆራረጥ እንዳጋጠማቸው ክላውድፍላር ራዳር አስታውቋል።
ባሳለፍነው መጋቢት ወር በበርካታ የምእራብ እና የደቡብ አፍሪካ ሀገራት ተመሳሳይ የሆነ የኢንርኔት መቆራረጥ ችግር አጋጥሞ እንደነበረ ይታወሳል።
ደቡብ አፍሪካ፣ ናይጄሪያ፣ አይቮሪ ኮስት፣ ላይቤሪያ፣ ቤኒን፣ ጋና እና ቡርኪና ፋሶ በወቅቱ የኢንተርኔት መቆራረጥ ከተከሰተባቸው አሀገራት መካከል ተጠቃሽ ናቸው።
በወቅቱ ተከተው ችግር ውቅያኖስ ውስጥ የተዘረጉ የኢንተርኔት መስመሮች ባልታወቀ ምክንያት በመቆረጣቸው እንደሆነ መገለጹ የሚታወስ ሲሆን፤ በሚሊየን የሚቆጠሩ ተጠቃሚዎችን ከፍተኛ የሆነ ጭንቀት እና ብስጭት ውስጥ ከቶ ነበር።