ቀጣዮቹን ሁለት ዓመታት በአባልነት ታገለግላለች
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት ጸጥታና ደህንነት ምክር ቤት አባል ሆና ተመረጠች
ኢትዮጵያ ከአስር የአፍሪካ ህብረት ጸጥታና ደህንነት ምክር ቤት አባል ሃገራት መካከል አንዷ ሆና ተመርጣለች፡፡ የተመረጠችው የህብረቱ ስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት በማድረግ ላይ ባለው ስብሰባ ባቀረበው ረቂቅ የእጩዎች ዝርዝር ሲሆን ቀጣዮቹን ሁለት ዓመታት (ከ 2012-2014 ዓ/ም) በአባልነት ታገለግላለች፡፡
በምርጫው ጅቡቲም ከምስራቅ አፍሪካ አባል ሆና ተካታለች፡፡ ካሜሩን፣ቻድ፣ግብጽ፣ማላዊ፣ሞዛምቢክ፣ቤኒን፣ጋና እና ሴኔጋልም በአባልነት ተመርጠዋል፡፡
ሆኖም ረቂቁ የፊታችን የካቲት 1 እና 2 በሚካሄደው የኅብረቱ የመሪዎች ጉባኤ መጽደቅ ይጠበቅበታል፡፡
የአባላት አመራረጥ
ምክር ቤቱ እኩል ድምፅ ያላቸው 15 አባላት አሉት፡፡ ከ15ቱ መካከል አምስቱ አባላት ለ3 ዓመታት ቀሪዎቹ 10 አባላት ደግሞ ለሁለት ዓመታት የሚመረጡ ናቸው።
ምርጫው የአህጉሪቱን ቀጣናዎች ታሳቢ አድርጎ የሚካሄድ ነው፡፡ሰሜን፣ደቡብ፣ምዕራብ እና ምስራቅ እንዲሁም ማዕከላዊ አፍሪካን ወክለው ሃገራት ይመረጣሉ፡፡ይህም የህብረቱን አባል ሃገራት ውክልና ሚዛናዊነት ለመጠበቅ እንደሚያስችል ይታመናል፡፡
በአባልነት ለመመረጥ በአዲስ አበባ ውጤታማ ዲፕሎማሲያዊ ቦታን ማግኘት እና መያዝ የግድ ይላል፡፡ በወታደራዊ እና በበጀት መዋጮዎች የተሻለ አፈጻጸም እና ፍላጎት ማሳየቱም ከመስፈርቶቹ መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
የምክር ቤቱ ተግባራት
የሰላምና ፀጥታ ምክር ቤቱ የህብረቱ አንድ አካል ሆኖ ህብረቱ የሚያሳልፋቸውን የተለያዩ ውሳኔዎች የሚያስፈጽም ነው፡፡በተለይ ከአህጉሪቱ ሰላምና ደህንነት ጋር የተያየዙ ግጭትን የመከላከል፣ የመቆጣጠር እና የመፍታት ኃላፊነትን አንግቡ ይንቀሳቀሳል፡፡
በተለያዩ ሃገራት ያሉ የሰላም ማስከበር ስራዎችም ይመለከቱታል፡፡
በሱዳን፣ሶማሊያ፣በቡሩንዲ እና በሌሎችም የአህጉሪቱ አካባቢዎች የተደረጉና የሚደረጉ ስምሪቶችም በምክር ቤቱ እዝ እና የቅርብ ክትትል የሚፈጸሙ ናቸው፡፡
ለሚከሰቱ ግጭቶች እና ቀውሶች ወቅታዊ እና ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚያስችል የደህንነት እና የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓትንም ዘርግቶ ይንቀሳቀሳል።