ኢትዮጵያ ስለምታመጥቃት ሳተላይት ምን ያህል ያውቃሉ?
በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያ የተባለችው ETRSS-1 አነስተኛ የመሬት ምልከታ ሳተላይት (Small Remote Sensing Satellite) በመጪው አርብ ታህሳስ 10 ቀን 2012 ዓ.ም. ማለዳ ወደ ህዋ እንደምትመጥቅ ተነግሯል፡፡
በቻይና መንግስት ድጋፍ በኢትዮጵያውያን የምህንድስና ጠበብቶች የተሰራችው ይህች ሳተላይት ከቤጂንግ 5 መቶ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከሚገኘው የቻይና ጠፈር ምርምር ማዕከል ነው ወደ ህዋ የምትመጥቀው፡፡ ለመሆኑ
የመሬት ምልከታ ማይክሮ ሳተላይት (Small Remote Sensing Satellite) ማለት ምን ማለት ነው?
በኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ተቋም ማህበራዊ ገጽ ላይ የሰፈረው መረጃ እንደሚያመለክተው
-መሬት ምልከታ (Remote sensing) ማለት፡
አንድን ቁስ ሳይነኩ ወይም አካላዊ ግንኙነት ሳይኖር ስለዛ ቁስ ከርቀት (ብርሀን ወይም ሙቀት በመጠቀም) መረጃዎችን መሰብሰብ ነው፡፡
ETRSS-1 ከመሬት 700ኪ.ሜ. ርቀት ላይ ሆና ስለ ኢትዮጵያ፣ ምስራቅና ምዕራብ አፍሪካ አካባቢ መረጃዎችን በመሰብሰብ እንጦጦ ህዋ ኦብዘርቫተሪ ማዕከል ወደሚገኘዉ መረጃ መቀበያ ጣቢያ ትልካለች፡፡
የመሬት ምልከታ መሳሪያዎች በሁለት ይከፈላሉ አክቲቭ እና ፓሲቭ (ACTIVE and PASSIVE) ተብለዉ፡፡
Active -የራሳቸዉን ሞገድ መረጃ ወደሚሰበሰብበት ቁስ በመልቀቅ ሲሰበስቡ (ለምሳሌ ወደ መሬት)
Passive - ተፈጥሮአዊ በሆነ መንገድ ከቁስ አካላት የሚመጣን መረጃ መበቀበል መረጃን ሲሰበስቡ ነው፡፡
የመሬት ምልከታ ማይክሮ ሳተላይት (Small Remote Sensing Satellite) እንዴት ይሰራል? ለምን ዓይነት ግልጋሎት ይዉላል?
ከላይ እንደተገለጸው የመሬት ምልከታ መሳሪያዎች ሙቀትን ወይም ብርሀንን በመጠቀም ስለመሬት ሁኔታ (አቀማመጥ፣ቀለም፣ቅርጽ፣መጠን) ፣ ስለ ዕጸዋትና እንስሳት (የብርቅዬ እንስሳት እንቅስቃሴ)፣ ስለ አየር ንብረት ሁኔታ፣ ስለዉሃማ አካላትና መሰል ጉዳዮች መረጃዎችን ያቀብላሉ፡፡
ከመሬት ምልከታ ሳተላይት የሚገኘዉ መረጃ ለተለያዩ የጥናትና ምርምር ዓይነቶች በግብዓትነት የሚያገለግል ነው፡፡
ለአየር ንብረት ትንበያ፣ ለግብርና (የአፈር ለምነት፣ የዝናብ ሁኔታ፣ ዘመናዊ ግብርና መከወን (Precision farming))፣ ለከተማ ዕቅድና ቅየሳ (የከተሞች መስፋፋት፣ ህገወጥ ቤቶች ግንባታ ቁጥጥር)፣ ለዉሃማ ኣካላት ቁጥጥር (የዉሃማ ኣካላት መድረቅ ወይም መስፋፋት)፣ ለካርታ ስራ፣ የተፈጥሮ ሀብት ቁጥጥር (ፓርኮችና በዉስጡ ስላሉ እንስሳትና እጽዋት)፣ ለግንባታ ስራዎች(የግድብ ስራዎች ዉሃ መጠን)፣ የተፈጥሮ አደጋዎች ትንበያ (ድርቅ፣ጎርፍ፣ መሬት መንቀጥቀጥ፣እሳት አደጋና መሰል ጉዳዮች)፣ ለትራንስፖርት ቁጥጥርና ዘመናዊነት፣ ለማዕድናት ጥናትና ፍለጋ እና ለሌሎችም የእድገት ዘርፎችየሚያገለግል ነው፡፡
በአፍሪካ የትኞቹ ሃገራት የመሬት ምልከታ ማይክሮ ሳተላይት አላቸው?
ከፈረንጆቹ 1998 ጀምሮ እስከያዝነው አመት ድረስ 8 የአፍሪካ ሃገራት 32 መሰል ሳተላይቶችን አምጥቀዋል፡፡ እነዚሁ ሃገራትም ደቡብ አፍሪካ፣ግብጽ፣ናይጄሪያ፣ጋና፣አልጄሪያ፣ሞሮኮ፣ኬንያ እና ሱዳን ናቸው፡፡
አንጎላም ሩሲያ ስሪት ያላትን ሳተላይት ለማምጠቅ ሞክራ ነበር ሆኖም ሙከራው ከ4 ወራት በኋላ እክል ገጥሞት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ ሳተላይቷም ጠፈር ላይ ሳለች ፈንድታለች፡፡ ይህን ለመካስም ሩሲያ በቀጣዩ የፈረንጆቹ ዓመት የምትወነጨፍ ተለዋጭ ሳተላይትን ለአንጎላ እየገነባችላት ነው፡፡
ከ32ቱ በተጨማሪም በዘርፉ የተሰማሩ የአህጉሪቱ ተቋማት ለ3 ተመሳሳይ ፕሮጄክቶች ድጋፍ አድርገዋል፡፡ ይህም የሳተላይት ቁጥሩን ወደ 35 ከፍ የሚያደርግ ነው እንደ አፍሪካ ስፔስ ኢንዱስትሪ ዓመታዊ ሪፖርት፡፡ ከ35ቱ 15ቱ በባለፉት 4 ዓመታት የመጠቁ መሆኑን ዘርፉ እያደገ ነው የሚለው ስፔስ ኢን አፍሪካ (Space in Africa) በ2019 ሪፖርቱ ተንትኗል፡፡ ከእነዚህ ሳተላይቶችም ውስጥ:-
14ቱ አነስተኛ የመሬት ምልከታ
10ሩ የግንኙነት
8ቱ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ሰርቶ ማሳያ እንዲሁም ቀሪዎቹ የሳይንሳዊ ምርምር የትምህርት እና ወታደራዊ አገልግሎትን የሚሰጡ ናቸው፡፡
በምድር ወገብ አቅራቢያ ለጠፈር ምልከታና ምርምር በሚመች የመሬት አቀማመጥ ላይ ትገኛለች የሚባልላት ኢትዮጵያም የእነዚሁን ሃገራት ጎራ ትቀላቀላለች፡፡ በቀጣይም የcommunication satellite ባለቤት መሆን ትችል ዘንድ ሰፊ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነዉ፡፡
የETRSS-1 ጥቅም
ለግብርናና ተያያዥ ግልጋሎቶች የሚውሉ የአየር ንብረት መረጃዎችን ትሰበስባለች
መረጃውን ተንትነው የሚያነቡ የሚያቀርቡም 20 መሃንዲሶች በቻይና ሰልጥነዋል
የሚገኘው ልምድ የተሻሻሉ ሳታላይቶችን በራስ አቅም ለመገንባት ያስችላል
ይህም የሳታላይት ኪራይ ወጪን ከማስቀረት በዘለለ ገቢን ለማመንጨት ያስችላል
ETRSS-1ን በተመለከተ የተደረጉ ዝግጅቶች
ሳተላይቷ ከቻይና ትወንጨፍ እንጂ የቁጥጥር እና መረጃን የመቀበያ ማዕከሏ በኢትዮጵያ የሚገኝ ነው፡፡
ማዕከሉ በእንጦጦ ህዋ ምልከታና ምርምር ጣቢያ የሚገኝም ሲሆን የመረጃ መቀበያ አንቴና እና መቆጣጠሪያ ተገንብተው ተጠናቀውለታል፡፡
ከ ETRSS-1 የሚገኙ መረጃዎችንን ተንትነው የሚያነቡና የሚያቀርቡ 20 መሃንዲሶችም በቻይና ሰልጥነው ዝግጁ ሆነዋል፡፡ ሳተላይቷ የምትመጥቅበትን ቀን በመጠባበቅ ላይም ይገኛሉ፡፡
ዘርፈ ብዙ ተያያዥ ፕሮጀክቶችን በማካሄድ ላይ መሆኑን ከሰሞኑ ለጎበኙት ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፤ የምክር ቤት አባላት እና ተማሪዎች የገለጸው የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴከኖሎጂ ኢንስቲትዩትም በአጭር ጊዜ ዉስጥ ለሃገር ኢኮኖሚያዊ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያለዉን የሳተላይት ፕሮጀክት ከዳር ለማድረስ ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ ላይ ስለመሆኑ አስታውቋል፡፡
በቀጣዮቹ 4 ዓመታት ውስጥ ሌሎች በዓይነታቸው የተለዩና የተሻሻሉ ሳተላይቶችን ለመገንባትም ከፈረንሳዩ የጠፈር ሳይንስ ተቋም አሪያና ግሩፕ ጋር ስምምነት ላይ ደርሷል፡፡