“የወጪ ንግድ (ኤክስፖርት) ባለፉት 10 ወራት 13 በመቶ አድጓል” ጠ/ሚ/ር ዐቢይ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኢትዮጵያን ያስመሰገነ ተቋም መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል
ዘንድሮ 9 በመቶ ያድጋል የተባለው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በኮሮና ምክንያት 6 በመቶ እንደሚያድግ ተገለጸ
“የወጪ ንግድ (ኤክስፖርት) ባለፉት 10 ወራት 13 በመቶ አድጓል” ጠ/ሚ/ር ዐቢይ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ5ኛው የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 5ኛ ልዩ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ከምክር ቤቱ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ የሆነው የኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ለመከላከል በመንግስት በኩል የሚከናወኑ ተግባራትን በተመለከተ ለተነሳላቸው ጥያቄ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ረዘም ያለ ሰዓት ወስደው ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ቫይረሱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ፣ ከዚያም ሲወርድ በአፍሪካ እና ኢትዮጵያ በምትገኝበት የምስራቅ አፍሪካ ንዑስ ቀጣና የሚያደርሰውን ተጽዕኖ እንደመንደርደሪያ ያብራሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ አስከፊ ወረርሽኝ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመከላከል እንዲሁም ቫይረሱ የሚፈጥራቸውን ዕድሎች በአግባቡ ለመጠቀም መንግስት በተደራጀ መንገድ ጠንካራ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡
የኮሮና ቫይረስ በአሁኑ ወቅት በሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮች በተለያየ መጠን መከሰቱን በማውሳት የፌደራል መንግስት ከበሽታው ጋር በተያያዘ በድምሩ 5 ቢሊዮን ብር መድቦ ለክልሎችም በድጎማ መልክ ማከፋፈሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አንስተዋል፡፡ ከተለያዩ ወዳጅ ሀገራት ሀብት በማሰባሰብ ከኢትዮጵያ ባለፈ ለመላው የአፍሪካ ሀገራትም በማከፋፈል የኢትዮጵያ መንግስት የላቀ የዓመራርነት ሚና መወጣቱን ተናግረዋል፡፡ በሁሉም ክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮች የኮሮና ቫይረስ ምርመራ የሚደረግባቸው የላቦራቶሪ ማዕከላት መቋቋማቸውን እና የሀገሪቱ የመመርመር አቅምም በየጊዜው እየጨመረ በአፍሪካ በመመርመር አቅማቸው ከፊት ለፊት ከሚጠቀሱ ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ እንድትሆን አስችሏታል ብለዋል፡፡ ይሁንና ኢትዮጵያ ካላት ህዝብ አንጻር የመመርመር አቅሟ ይበልጥ ሊጨምር እንደሚገባም ነው ያነሱት፡፡
የጤና ተቋማትን ዝግጅት በመመለከት በሰጡት ማብራሪያ እስካሁን በመንግስት በኩል ከ17 ሺ በላይ የኮሮና ተጠቂዎችን ለማከም የሚያስችሉ 54 የህክምና ማዕከላት መቋቋማቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡ 30 ሺ ገደማ የሚሆኑ ምልክት የታየባቸውን ሰዎች ለይቶ ለማቆየት የሚያስችል ማቆያ እንዲሁም ከውጭ ሀገራት ለሚመለሱ ለ45 ሺ ሰዎች የሚሆን ለይቶ ማቆያ መዘጋጀቱንም ጠቁመዋል፡፡
ከተለያዩ ሀገራት ተገፍተውም ይሁን ፈልገው የሚመለሱ ዜጎችን ተቀብሎ በማስተናገድ ረገድ ኢትዮጵያ የተሻለ ኢኮኖሚ ካላቸው በርካታ ሀገራት የተሻለ ስራ በማከናወን ላይ ትገኛለች ሲሉም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የመንግስታቸውን ተግባር የገለጹት፡፡ ይሄም ዜጋ ተኮር ፖሊሲ መከተላችንን ብቻ ሳይሆን ለዜጎች ቅድሚያ የሰጠ ተግባር እያከናወንን መሆኑን የሚያመለክት ነውም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
የኮሮና ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ
በ2012 ዓ.ም የበጀት ዓመት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ 9 በመቶ ለማሳደግ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም ኮሮና ቫይረስ በፈጠረው ተጽዕኖ ምክንያት በታቀደው ልክ ማስመዝገብ ባይቻልም ቢያንስ 6 በመቶ ዕድገት እንደሚመዘገብ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡ ከ170 በላይ የዓለማችን ሀገራት የኢኮኖሚ ዕድገታቸው ከዜሮ በታች ቁልቁል ወደታች እንደሚወርድ በተተነበየበት በዚህ ጊዜ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ 6 በመቶ ማደግ መቻሉ የሚያበረታታ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም አይኤምኤፍም ቢሆን ሀገሪቱ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ከ3 በመቶ በላይ ዕድገት እንደምታስመዘግብ መተንበዩንም አንስተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ለምን ክፉኛ አልተጎዳም?
የሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት በከፍተኛ ደረጃ ላለመጎዳቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምክንያትነት ያነሱት ዋነኛው ጉዳይ የበጀት ዓመቱ የሚጀመርበት ወቅት ነው፡፡ እናም የበጀት ዓመቱ ከተጀመረበት ከሀምሌ ወር አንስቶ ለ8 ተከታታይ ወራት የወጪ ንግድ (ኤክስፖርት) ከታቀደው በላይ መሄዱን እና በቫይረሱ ምክንያት ቅናሽ የታየው ባለፉት 4 ወራት ብቻ መሆኑን በዝርዝር ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም የኤክስፖርት ገቢው ጠንካራ መሆኑ ኢኮኖሚው እንዳይጎዳ ከፍተኛውን አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፡፡
ባጥቅሉ ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ እያሽቆለቆለ ከነበረበት በመነሳት ፣ ዘንድሮ የሀገሪቱ ኤክስፖርት ከ13 በመቶ በላይ ዕድገት እንዳስመዘገበ ነው ያብራሩት፡፡ ዋነኛ እድገት ያስመዘገቡ ዘርፎችን በዝርዝር የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፉት 10 ወራት በቡና ኤክስፖርት 667 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱን እና ይሄም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ16 በመቶ ብልጭ ማሳየቱን ተናግረዋል፡፡ ሌላው ከኮሮና መከሰት ጋር ተያይዞ ለኢትዮጵያ የተሸለ ዕድል የተፈጠረው በአበባ ኤክስፖርት መስክ ሲሆን ከዘርፉ 440 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱን ፣ ይሄም በማይታመን መልኩ የ84 በመቶ እድገት ያሳየ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ የሥጋ ፍላጎትም ከውጭ ሀገራት በከፍተኛ መጠን እየጨመረ እንደሆነና ባለፉት 10 ወራት 45 ሚሊዮን ዶላር ከሥጋ ኤክስፖርት መገኘቱን ገልጸዋል፡፡ ይሄም የ21 በመቶ ዕድገት ያሳየ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወርቅና ሌሎች ማዕድናትም የተሸለ ገቢ እየተገኘ ነው ብለዋል፡፡
ኢኮኖሚው ክፉኛ ላለመጎዳቱ ሁለተኛው ምክንያት የሀገሪቱ የንግድ ስርዓት ከዓለም ጋር ያለው ትስስር ከ30 በመቶ በታች መሆኑ ሲሆን የፋይናንስ ዘርፉ አለመጎዳትም ሌላው ምክንያት ነው እንደጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ፡፡ የባንኮች ተቀማጭ ገንዘብ እየጨመረ ከመሆኑም ባለፈ የሚበላሽ ብድር መጠናቸው በከፍተኛ መጠን መቀነሱን እንዲሁም ተመላሽ ብድር መጨመሩም የፋይናንስ ዘርፉ እንዳይጎዳ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ምክንያቶች ናቸውም ብለዋል፡፡ መንግስት ባንኮችን ለመደጎም 13 ቢሊዮን ብር ፈሰስ ማድረጉንም አንስተዋል፡፡
በኢኮኖሚው ላይ ጉልህ ሚና ያላቸው እንደ ነዳጅ ያሉ አንዳንድ የገቢ (የኢምፖርት) ምርቶች ዋጋ መቀነስም ኢኮኖሚውን በመደጎም ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ቢያነሱም በሌላ መልኩ የማዳበሪያ እና አንዳንድ ሸቀጦች ዋጋ መጨመር ደግሞ ጉዳት እንዳላቸውም ተናግረዋል፡፡
ለጉዳት የተጋለጡ ዘርፎች እና መፍትሔያቸው
ቱሪዝም እና የአገልግሎት ዘርፎች በከፍተኛ መጠን ቢጎዱም ከኮሮና ወረርሽኝ በኋላ እነዚህ ዘርፎች ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጠቀሜታ እንዲኖራቸው እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡ የእንጦጦ ፓርክ እና የወንዝ ዳርቻ ፕሮጄክት ከአንድነት ፓርክ ጋር ተዳምረው ቱሪዝሙን ለማነቃቃት እና ከፍተኛ የገቢ ምንጭ ለማድረግ በአዲስ አበባ ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል እንደሆኑ በመጥቀስ በቀጣይነትም ለቱሪዝም ዘርፍ መንግስታቸው ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሰጥም ተናግረዋል፡፡ ከኮሮና በኋላ ከፍተኛ የቱሪስት መዳረሻ ከሚኖራቸው ቀዳሚ የዓለማችን ሀገራት ተርታ ኢትዮጵያ የተቀመጠችው በነዚህ ምክንያቶች እንደሆነም አውስተዋል፡፡
የምግብ እጥረት እንዳይከሰት በሚል መንግስት የሚያደርገው የጥንቃቄ እርምጃ በተለያየ መልኩ እየጨመረ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ 3.2 ቢሊዮን ብር ወጪ በማድረግ የስንዴና ዘይት ግዢ መፈጸ ሙን ተናግረዋል፡፡ በማዕድ ማጋራት እንቅስቃሴም ህብረተሰቡ 1.8 ቢሊዮን ብር የሚገመት እርዳታ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ በመላ ሀገሪቱ በሺዎች የሚቆጠሩ የምግብ ባንኮች መዘጋጀታቸውንም ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተለያዩ ለጋሽ እና አበዳሪ ተቋማት እንዲሁም መንግስታት 2 ቢሊዮን ዶላር ያህል ገንዘብ መገኘቱንም ነው የተናገሩት፡፡
ወረርሽኙን ወደ መልካም አጋጣሚ የሚቀይረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ
ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በተያያዘ አየር መንገዱ እንደሌሎች በርካታ የዓለማችን ስመጥር እና ግዙፍ አየር መንገዶች ሳይንገራገጭ ስራውን በአግባቡ እያከናወነ መሆኑን ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የተናገሩት፡፡ አየር መንገዱ ሰራተኞችን ሳይቀንስ፣ ደሞዛቸውንም ሳይቀንስ ፣ ያለበትን እዳም እየከፈለ ቢሆንም ከመንግስት ምንም ድጎማ እንዳልተደረገለት ጠቁመዋል፡፡ ባለፉት ሶስት ወራት ብቻ አየር መንገዱ 15 ቢሊዮን ብር ወጪ ማድረጉንም ነው የተናገሩት፡፡ የመንገደኞች አውሮፕላኖችን ወደ ካርጎ አውሮፕላን በመቀየር የሚያከናውነው ተግባርም የአየር መንገዱን የአስተዳደር ኃላፊዎች እና ጠቅላላ ሰራተኞችን የሚያስመሰግን ነው ብለዋል፡፡ ከተለያዩ ሀገራት መሪዎች ጋር በሚያደርጉት ውይይትም በአየር መንገዱ ጠንካራ ስራ ምክንያት ለኢትዮጵያ መንግስት ምስጋና ማቅረባቸውን በመጥቀስ አየር መንገዱ በዓለም ላይ ስመጥር አየር መንገድ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የእርዳታ ቁሳቁሶች ማከማቻና ማከፋፈያ ማዕከል እንድትሆን መወሰኑም በአየር መንገዱ ላይ ሙሉ እምነት በመጣሉ ነው ብለዋል፡፡ አየር መንገዱ በኮሮና ወቅት በረራ እንዲያቆም ይደረግ የነበረው ዘመቻ በበርካታ ምክንያቶች ስህተት መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አየር መንገዱ ስራውን በመቀጠሉ በርካታ ውጤት ያስመዘገበ ሲሆን በጉዳት ደረጃ ሊታይ የሚችለው 5 ሰራተኞቹ በቫይረሱ መያዛቸው ነው ብለዋል፡፡ ይሁንና እነዚህ 5 ሰራተኞችም ከቫይረሱ ሙሉ በሙሉ እንዳገገሙ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
ኮሮና ፣ ቻይናና የኢትዮጵያ አየር መንገድ
በቻይና የኮሮና ቫይረስ በተከሰተበት ወቅት በሀገሪቱ የሚገኙ ኢትዮጵያያን ተማሪዎችን መንግስት እንዲመልስ ፣የሌሎችን ሀገራት ተሞክሮ በማንሳት እና ከነሱ ጋር በማወዳደር በርካታ ዘመቻ ቢደረግም መንግስት ተማሪዎችን ከመመለስ ይልቅ ባሉበት ጥበቃ እንዲደረግላቸው ከቻይና መንገስት ጋር በመነጋገር መስራቱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡ በዚህም ቻይና ለተማሪዎቹ ከፍተኛ ጥበቃ በማድረጓ አንድም ኢትዮጵያዊ ተማሪ በቫይረሱ አለመያዙን በመግለጽ ለቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቻይና በተገለለች እና በአስቸጋሪ ወቅት ላይ በነበረችበት ጊዜ ወደ ሀገሪቱ የሚያደርገውን በረራ አለማቋረጡ ዛሬ አየር መንገዱ የተሸለ ተጠቃሚ እንዲሆን እንዳደረገው ጠቅላይ መኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናግረዋል፡፡ ቻይና ከሌሎች አየር መንገዶች በተለየ መልኩ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ አሁን ላይ በሳምንት 90 በረራ እንዲያደርግ መፍቀዷንም ከዚሁ ጋር አያይዘው ተናግረዋል፡፡
የመንግስት ቀጣይ ትኩረቶች
በቀጣይነት መደረግ ያለበትን ጥንቃቄ በተመለከተ ከበሽታው መጠንቀቅ እና ተገቢዉን የመከላከል ስራ በትኩረት ማከናወን ፤ የግብርና ስራን በስፋት በማከናውን ትርፍ ማምረት ፤ ከኮሮና በኋላ ባለው ዓለም በሁሉም ዘርፍ ተወዳዳሪ ለመሆን መስራት ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫዎች ናቸው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፡፡