
የሁሉንም መንገደኞች የሰውነት ሙቀት የመለየት ስራ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተጀምሯል
የኮሮና ቫይረስ ልየታ ስራ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮላፕላን ማረፊያ ተጀመረ
ኢትዮጵያ ኖቭል ኮሮና ቫይረስ ወደ ሀገሯ እንዳይገባ ለመከላከል የሚያስችል ዝግጅት ማድረጓን የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡
ቫይረሱ ቀደም ብሎ የሚታወቅ በሽታ አምጭ ተኅዋስ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት የተከሰተው ግን አዲስ የቫይረስ ዓይነት እንደሆነ ተጠቁሟል ያለው ኢንስቲትዩቱ በኢትዮጵያ በኩል ያለውን ዝግጁነት በተመለከተ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
ኢንስቲትዩቱ ኢትዮጵያ ከተለያዩ ሀገራት ጋር የአየርና የየብስ ትራንሰፖርት ትስስርን ታደርጋለች፤የኢትዮጵያ አየር መንገድም በ5 የተለያዩ የቻይና ግዛቶች በሳምንት 35 በረራዎችን ያደርጋል ያለ ሲሆን የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል ወደ ሃገር ለሚገቡ ለሁሉም መንገደኞች የሰውነት ሙቀት ልየታ ስራ በቦሌ ዓለም አቀፍ አአውሮፕላን ማረፊያ መጀመሩን አስታውቋል።
የዓለም ጤና ድርጅት ቫይረሱ ከታሕሳስ 21፣2012 ዓ.ም. ጀምሮ በቻይና ዉሃን ክልል የተከሰተ መሆኑን ያስታወቀ ሲሆን እስከ ዛሬ ማለትም ጥር 15, 2012 ዓ.ም. ድረስ በጠቅላላ አምስት መቶ ሰማንያ አንድ (581) ታማሚዎች እንዳሉ ሪፖርት ተደርጓል፡፡
አምስት መቶ ሰባ አንድ (571) የሚሆኑት ታማሚዎች ከቻይና ብቻ ሪፖርት የተደረጉ ሲሆን ከነዚህም ታማሚዎች ውስጥ 17 የሚሆነት ህይወታቸው አልፏል፡፡
በቻይና በመጀመሪያ የበሽታው ምልክት የታየው በውሃን ከተማ በሚገኝ የባሕር ምግብ ገበያ የባሕር ምግቦችን የሚያዘጋጁና የሚያቀርቡ ሰዎች ላይ ሲሆን በሽታው ወደ አሜሪካ፣ ጃፓን፣ ታይላንድ፣ ኮሪያ ሪፐብሊክ እና ሲንጋፖር ከቻይና በተነሱ ተጓዦች አማካኝነት መስራጨቱ ታውቋል፡፡