የኢትዮጵያ አየር መንገድ የዓለም ሴቶች ቀንን አስመልክቶ በሴቶች ብቻ የተመራ በረራ አደረገ
በካፒቴን ቃልኪዳን ግርማ የተመራው ይህ በረራ ከአዲስ አበባ ወደ ለንደን በዛሬው ዕለት ተደርጓል
ካፒቴን ቃልኪዳን ግርማ የመጀመሪያዋ ሴት ኤርባስ A350 አውሮፕላን አብራሪ ተብላለች
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የዓለም ሴቶች ቀንን በማስመልከት በሴቶች ብቻ የተመራ በረራ አደረገ፡፡
በየዓመቱ የሚከበረው የዓለም ሴቶች ቀን በፈረንጆቹ መጋቢት ስምንት ቀን ይከበራል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ይህንን በዓል አስመልክቶ ሙሉ ለሙሉ በሴቶች ብቻ የተመራ በረራ አካሂዷል፡፡
ከአዲስ አበባ-ለንደን ሂትሮው ኤርፖርት የተደረገው ይህ በረራ በመጀመሪያዋ የኤርባስ A350 አውሮፕላን አብራሪ ቃልኪዳን ግርማ አማካኝነት እንደተደረገ አየር መንገዱ ለአልዐይን አስታውቋል፡፡
ካፒቴን ቃልኪዳን በረራውን አስመልክቶ እንዳለችው “ሙሉ ለሙሉ በሴቶች ብቻ የተመታ በረራ በማድረጋችን ደስተኛ ነኝ፣ ይህ በረራ የጾታ እኩልነትን ለመፍጠር ከመርዳቱ ባለፈ ሴቶች ወደ አቪዬሽን ሙያ እንዲገቡ ያበረታታል” ብላለች፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው በበኩላቸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሙሉ ለሙሉ በሴቶች ብቻ የተመራ በረራ ያደረጉት አየር መንገዱ ስኬታማ እንዲሆን ሴቶች ላደረጉት ጥረት እውቅና ለመስጠት ታስቦ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ሴት የአቪዬሽን ባለሙያዎችን ለማፍራት ታስቦ ይህ ልዩ በረራ ተዘጋጅቷል ያሉት አቶ መስፍን በተቋማችን እያንዳንዱ ስራችን ውስጥ የሴቶች ሚና ከፍተኛ መሆኑም አክለዋ፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከዘጠኝ ዓመት በፊት አንስቶ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን በማስመልከት ሙሉ ለሙሉ በሴቶች የታገዘ በረራ ወደ ተለያዩ ሀገራት በማካሄድ ለይ ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግዙፉን ቦይንግ 777X-9 አውሮፕላኖችን ከቦይንግ ኩባንያ ለመግዛት የሚያስችለውን ስምምነት ከሰሞኑ መፈራረሙ ይታወሳል።
አየር መንገዱ የቦይንግ አዲስ ምርት የሆኑትን በቅርብ ግዜ እና በሂደት የሚረከባቸውን የ20 ቦይንግ 777X-9 አውሮፕላኖችን ለማስገባት የሚያስችለውን ስምምነት ባሳለፍነው ማክሰኞ ከቦይንግ ጋር ተፈራርሟል።
በስምምነቱ መሰረት አየር መንገዱ ለመግዛት የፈረመባቸው 8 አውሮፕላኖችን የሚረከበው በፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ2027 ጀምሮ እስከ 2030 ድረስ መሆኑም የተጠቁሟል።