በቶኪዮ ማራቶን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ትልቅ የማሸነፍ ግምት አግኝተዋል፡፡
የዓለም አትሌቲክስ የፕላቲነም ደረጃ በሚሰጠው የቶኪዮ ማራቶን እስካሁን ከተደረጉ 13 ውድድሮች በወንዶች 4 በሴቶች 6 ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አሸንፈዋል፡፡ የቦታው ክብረ ወሰን የተያዘው ግን በኬንያውያን አትሌቶች ነው፡፡
በመጪው የአውሮፓውያኑ መጋቢት 1 በሚጀመረው በዚህ የማራቶን ውድድር ኢትዮጵያውያኑ ብርሃኑ ለገሰ እና ሩቲ አጋ ያሸንፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የዓለም አትሌቲክስ ዘገባ ያሳያል፡፡
ብርሃኑ ለገሰ በ2019 ቶኪዮ ላይ ርቀቱን በ2፡04፡48 በማጠናቀቅ ሲያሸንፍ በዚሁ አመት በርሊን ማራቶን ላይ ኤሉድ ኪፕቾጌን 2፡02፡48 በሆነ ሰዓት ተከትሎ ገብቷል፡፡ ይህም ምርጥ የግል ሰዓት ሆኖ ተመዝግቦለታል፡፡ሆኖም በቶኪዮው ውድድር ልክ እንደ ብርሃኑ ሁሉ ርቀቱን ከ2 ሰዓት ከ05 ደቂቃ በታች የገቡ ስምንት አትሌቶች መኖራቸው ፉክክሩን ከፍ እንደሚያደርገው ይጠበቃል፡፡
የዱባይ ማራቶን አሸናፊው ጌታነህ ሞላ፣ሲሳይ ለማ፣አሰፋ መንግስቱ እና ኃይሌ ለሚ ኢትዮጵያውያን የብርሃኑ ተቀናቃኞች ናቸው፡፡የውድድሩ የሁለት ጊዜ አሸናፊ ኬንያዊው ዴክሰን ቹምባ በተመሳሳይ የአሸናፊነቱን ቅድመ ግምት አግኝቷል፡፡የዓለም ሻምፒዮና የነሃስ ሜዳሊያ ባለቤቱ አሞስ ኪፕሩቶ እና ቤዳን ካሮኪምም የውድድሩ ተሳታፊዎች ናቸው፡፡
ልክ እንደ ብርሃኑ ሁሉ ኢትዮጵያውያኑ ሴት አትሌቶችም በፉክክሩ ይጠበቃሉ፡፡ የውድድሩ የባለፈው ዓመት አሸናፊ ሩቲ አጋ ክብሯን ለማስጠበቅ እንደምትሮጥ ይጠበቃል፡፡ሩቲ 2፡20፡40 ነበር ርቀቱን ያጠናቀቀችው፡፡ ከ2 ዓመት በፊት በበርሊን ማራቶን 2፡18፡34 በመግባት ሁለተኛ ወጥታ ነበረ፡፡ ሰዓቱም ምርጥ የግል ሪከርዷ ነው፡፡
የውድድሩ የ2015 እና 2018 አሸናፊዎቹ ብርሃኔ ዲባባ እና ትርፌ ጸጋዬ ሩቲን ለመፎካከር ቅድመ ግምትን አግኝተዋል፡፡ ብርሃኔ ባሳለፍነው ወር ስፔን ቫሌንሺያ ላይ ሶስተኛ ስትወጣ የገባችበት 2፡18፡46 ምርጥ የግል ሰዓቷ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ በውድድሩ የኢትዮጵያ የግማሽ ማራቶን የክብረ ወሰን ባለቤት ሰንበሬ ተፈሪም ትሳተፋለች፡፡
የቶኪዮ ማራቶን ከባድ ፉክክር የሚጠበቅበት ብቻም ሳይሆን የተሻለ ሰዓት የሚያስመዘግቡ ጃፓናውያን አትሌቶች ለኦሎምፒክ የሚመለመሉበት ነው ተብሏል፡፡