ኢትዮጵያና ቻይና ትብብራቸውን ይበልጥ ለማጠናከር ተስማሙ
በኢፌዲሪ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ የተመራ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ከሰሞኑ በቻይና የ4 ቀናት የስራ ጉብኝት አድርጓል፡፡
የልዑካን ቡድኑ በቆይታው ከቻይና የኢንዱስትሪና ንግድ ባንክ (ICBC)፣ ከቻይና የወጭ ንግድና ብድር ዋስትና ኮርፖሬሽን (SINOSURE)፣ ከቻይና ብሄራዊ ልማትና ሪፎርም ኮሚሽን (NDRC)፣ ከቻይና ንግድ ሚኒስቴር (MOFCOM)፣ ከቻይና ወጭና ገቢ ባንክ (EXIM Bank)፣ ከቻይና ልማት ባንክ (CDB) እና ቻይና- አፍሪካ ልማት ፈንድ (CADFund) ከፍተኛ የመንግስት ሃላዎች ጋር ተገናኝቶ በሁለቱ አገራት የልማት ትብብር ዙሪያ ውይይት አድርጓል።
የልዑክ ቡድኑ በኢትዮጵያ ያለውን ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የማህበራዊ ለውጥ ለቻይና ባለስልጣናትና ለተቋማቱ ኃላፊዎች ያስረዳ ሲሆን፥ በዚህ ታሪካዊና ወሳኝ ወቅት የቻይና መንግስት ለውጡን በተጠናከረ መንገድ እንዲደግፍ ጠይቋል።
ሁለቱ አገራት በቻይና አፍሪካ ፎረም (FOCAC)፣ በቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሸቲቭ፣ በሁለቱ ሀገራት መካከል በተመሰረተው ሁሉን አቀፍ ስትራቴጅያዊ ትብብር እና ውጤታማ የአቅም ግንባታ ትብብር ማዕቀፎች በመመስረት በሚቀጥሉት 3 ዓመታት የሚኖረው የልማትና የኢንቨስትመንት ትብብር ከምንጊዜውም በተሻለ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተስማምተዋል።
አቶ አህመድ ሺዴ ከላይ ከተጠቀሱት ተቋማት በተጨማሪ ኢትዮጵያ ውስጥ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን እየሰሩ ካሉና ለመስራት በእንቅስቃሴ ላይ ከሚገኙ የመንግስትና የግል ኩባንያዎች ኃላፊዎች ጋርም ተወያይተዋል።
በውይይቱም እየተካሄዱ ያሉ ፕሮጀክቶች ውጤታማ ሆነው በሚጠናቀቁበት ሁኔታ ላይ መግባባት ላይ መደረሱንና ባለሃብቶቹ የመንግስትን የኢኮኖሚ ሪፎርም ተከትሎ ወደ ግሉ ይዞታ በሚተላለፉ ፕሮጀክቶች ላይም እንደሚሳተፉ መገለፁን ከኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።