የህዳሴውን ግድብ በተመለከተ በዋሽንግተን ሲደረግ የነበረው ድርድር በስምምነት ተጠናቀቀ፡፡
በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ሲደረግ የነበረው ድርድር ተጠናቀቀ
የኢትዮጵያ፣የግብጽና የሱዳን የውጭ ጉዳይና የውሃ ሚኒስትሮች በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ሲያደርጉት የነበረው ድርድር መጠናቀቁን የኢትዮጵያ የውኃ መስኖና ኢነርጅ ሚኒስትር ስለሽ በቀለ አስታውቀዋል፡፡
ሚኒስትሩ በትዊተር ገጻቸው እንደገለጹት ሶስቱ አገራት የዓለም ባንክና የአሜሪካ ተወካዮች በተገኙበት ግድቡን በተመለከተ ሲያደርጉት በነበረው ድርድር ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
ሁሉም አካላት በተገኙበት የተደረገው ድርድሩ በፈረንጆቹ አቆጣጠር ከጥር 13- 15 የተካሄደ ሲሆን በግድቡ የውሃ አሞላል ዙሪያ በትብብር ለመስራት እና በዘላቂነት ሁሉንም ወገኖች ተጠቃሚ ለማድረግ ከሚያስችል ስምምነት ላይ መደረሱ ተገልጿል፡፡
ይህንኑ በማስመልከትም በታዛቢነት የተሳተፉትን የአሜሪካ ትሬዠሪ ዲፓርትመንትና የዓለም ባንክን ጨምሮ 3ቱ ተደራዳሪ ሃገራት የጋራ መግለጫ አውጥተዋል፡፡ በመግለጫው መሰረትም በተከታዮቹ 6 ነጥቦች ስምምነት ላይ መደረሱ ይፋ ሆኗል፡፡
ስምምነት የተደረሰባቸው ነጥቦች
1. የኢትዮጵያ የታላቁ የህዳሴ ግድብ ውሃ አሞላል ደረጃ በደረጃ፤በትብብር መንፈስ የሚከናወን ሆኖ አጠቃላይ የዓባይ ውሃ ሁኔታዎች እየታዩ በታችኛው የተፋሰሱ ሃገራት ያሉ የውሃ ማከማቻ የአሞላል ሁኔታ ከግምት አስገብቶ የሚከናወን ይሆናል
2. ሙሌቱ በክረምት ወራት ማለትም ከሃምሌ እስከ ነሃሴ የሚከናወን ሲሆን እንደ ሁኔታው እስከ መስከረምም ሊቀጥል ይችላል
3. የሙሌቱ የመጀመሪያ ደረጃ ከባህር ጠለል በላይ 595 ሜትር ከፍታን በቶሎ ለመሙላት እና ኤሌክትሪክ ማመንጨት ለመጀመር በሚያስችል ነገር ግን ግብጽ እና ሱዳን በከፋ የድርቅ ወቅት ሊገጥማቸው የሚችለውን ችግር በሚያቀል መልኩ ይከናወናል፡፡
4. የሙሌቱ ተከታታይ ደረጃዎች የዓባይ ውሃ ሁኔታዎችን እና የግድቡን ደረጃ ታሳቢ አድርገው የኢትዮጵያን ግድቡን የመሙላትና ኤሌክትሪክ የማመንጨት ፍላጎቶች እንዲሁም ሊደረስ በሚችለው የውሃ አለቃቀቅ ስምምነት መሰረት ግብጽ እና ሱዳን በድርቅና በተራዘሙ የድርቅ ወራት ሊገጥሟቸው ለሚችሉ ችግሮች ተገቢውን ግምት ሰጥተው የሚፈጸሙ ይሆናል፡፡
5. የግድቡ የረዥም ጊዜ ትግበራ ግድቡ የዓባይ ውሃን ሁኔታ እና የግድቡን ደረጃ ታሳቢ አድርጎ የውሃ አለቃቀቁን ሊወስንና ኤሌክትሪክ ሊያመነጭና ግብጽ እና ሱዳን ዝናብ በማይዘንብባቸው የተራዘሙ አመታት፣በድርቅ እና በተራዘመ ድርቅ ሊገጥሟቸው የሚችሉ ችግሮችንም ከግምት ውስጥ አስገብቶ ይከናወናል፡፡
6. አለመስማማትን ሊያስቀሩ የሚችሉ ውጤታማ የትብብር መንገዶች እና አቅርቦቶች ይመቻቻሉ፡፡
ሚኒስትሮቹ ድርቅንና የተራዘመ ድርቅን በተመለከተ የጋራ ሃላፊነት እንደሚኖራቸው ተስማምተዋል፡፡ በድጋሚ ጥር 28 እና 29 በዋሸንግተን ዲሲ ተገናኝተውም በቀሪ የስምምነቱ ጉዳዮች ማለትም በሙሌቱ እና በቴክኒክና የህግ ጉዳዮች ላይ እንደሚመክሩም መግለጫው ይጠቁማል፡፡
ስምምነቱ ሊያስገኝ ለሚችለው ቀጣናዊ ጥቅም እውቅና የሰጡት ሚኒስትሮቹ በኢትዮጵያ የሚገነባው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ትብብርን በማጠናከር፣ቀጣናዊ ልማትና ምጣኔ ሃብታዊ ውህደትን በማምጣት ረገድ የጎላ አበርክቶ እንዳለውም ተስማምተዋል፡፡ ድንበር ዘለል ትብብር ማድረጉ የህዝባቸውን ኑሮ ለማሻሻል እንደሚበጅም ነው ስምምነቱን ከዳር ለማድረስ ያላቸውን ቁርጠኝነት ያስታወቁት የ3ቱ ሃገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የገለጹት፡፡