ከአሜሪካ የሰላም እቅድ በኋላ እስራኤል በጋዛ የአየር ድብደባ ፈጸመች
ከአሜሪካ የሰላም እቅድ በኋላ እስራኤል በጋዛ የአየር ድብደባ ፈጸመች
አሜሪካ አወዛጋቢውን “የመካከለኛው ምስራቅ የሰላም እቅድ” ይፋ ማድረጓን ተከትሎ እስራኤል በጋዛ በሚገኘው የፍሊስጤም ወታደራዊ የጦር ሰፈር ላይ የአየር ድብደባ መፈጸሟን ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡
በትናንትው እለት ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ አዋጭ ነው ያሉትን “የሁለት ሀገራት መፍትሄ” የሰላም እቅድ ይፋ አድርገው ነበር፡፡ ነገርግን የእቅዱ ይዘት ሲታይ ለእያንዳንዱ የእስራኤል ፍላጎት የቀረበ ሲሆን፣ ፍሊስጤማዊያን እቅዱን ወዲያዉኑ ተቃውመውታል፡፡
እቅዱ እስራኤል በሰፈራ የያዘቻቸውን የዌስት ባንክ ሰፈራ ቦታዎችን ወደ ግዛቷ እንድታጠቃልልና፣ ፍሊስጤም ደግሞ ሉአላዊ ግዛቷን በመቀነስ ሀገር እንደምትሆን አሻግሮ የሚያመላክት መሆኑ ተነግሯል፡፡
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኒታኒያሁ ዌስት ባንክ ያሉት የሰፈራ ቦታዎች በመጠቅለል የመጀመሪያ እርምጃ እንደሚወስዱ ባለፈው እሁድ ገልጸው ነበር፡፡
ይህን ተከትሎም የእስራኤል ጦር በዌስት ባንክና በጋዛ አካባቢ የወታደር ስምሪት እንዲጨምር ተደርጓል፡፡
እስራኤል በወታደራዊ ሰፈሮችና መገልገያዎች ላይ የአየር ድብደባውን ያካሄደችው ቀደም ብሎ ወደ ግዛቷ ሮኬት በመተኮሱ ምላሽ ለመስጠት ነው ተብሏል፡፡ ሁለት ተከታታይ የአየር ድብደባዎች በሰሜናዊና በደቡባዊ የጋዛ ሰርጥ ላይ የአየር ድብደባ መፈጸሙ የታወቀ ቢሆንም እስካሁን ምንም ጉዳት አልደረሰም፡፡
በእስራኤል ላይ ለተተኮሰው ሮኬት ኃላፊነት የወሰደ አካል ባይኖርም፤ የእስራኤል ጦር በአካበቢው የሚንቀሳቀሰው ሀማስ ሀላፊነቱን ይወስዳል ብሏል፡፡