ጃፓን ሕጉን ባለመቃወም ከሩሲያ ጋር ያበረች ሁለተኛዋ ባለግዙፍ ኢኮኖሚ የቻይና ወዳጅ ሀገር ሆናለች
ጃፓን ሕጉን ባለመቃወም ከሩሲያ ጋር ያበረች ሁለተኛዋ ባለግዙፍ ኢኮኖሚ የቻይና ወዳጅ ሀገር ሆናለች
የቻይና ምክር ቤት ሆንግ ኮንግን የሚመለከተውን ሕግ ማጽደቋን ተከትሎ ወቀሳዎች እየደረሱባት ቢሆንም ይህንን ግን እንደማታወግዝ ጃፓን አስታወቀች። አሜሪካ፣ብሪታንያ፣ ካናዳና አውስትራሊያ ግን ቤጂንግ በራስ ገዟ ሆንግ ኮንግ ያወጣችውን ሕግ ተቃውመዋል። ቶኪዮ በጉዳዩ ላይ ተቃውሞ ካላቸው ዋሽንግተን ኦታዋና ካንቤራ ጋር አልሰለፍምም ብላለች። ይሁንና የጃፓን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በጃፓን የአሜሪካ ኤምባሲ በጉዳዩ ላይ አስተያየት አልሰጡም ተብሏል፡፡
ቻይናና ሆንግ ኮንግ በአንድ ሀገር ሁለት ሥርዓት የሚል የቆየ ስምምነት ያላቸው ሲሆን ሆንግ ኮንግ ከሌሎች የቻይና ግዛቶች የተለየ ነጻነትና አስተዳደር አላት፡፡ ለ99 ዓመታት በሊዝ ውል ለብሪታኒያ ተሰጥታ የነበረቸው ሆንግ ኮንግ የውሉ ጊዜ ሲጠናቀቅ በአውሮፓውያኑ 1997 ወደ ቻይና ተቀላቀለች፡፡ በወቅቱ ወደ ቻይና ስትመለስ ልዩ አስተዳደር ክልል ሆና ነበር፡፡
በዚህም መሰረት አንድ ሀገር ሁለት ሥርዓቶች (one country two systems) በሚል ቤጂንግና ሆንግ ኮንግ ቀጠሉ፡፡ የተለየችው ግዛት ሆንግ ኮንግ የራሷ ሕግ አውጭ፣ ሕግ አስፈጻሚና ሕግ ተርጓሚ አላት፡፡ ይሁንና የራሷ ወታደራዊ ተቋምና በመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታ ምክር ቤት ተወካይ የላትም፡፡ ከዚያ በመለስ ግን የተለየ ነጻነት አላት፡፡
ግዛቲቱ ታዲያ በርካት የጸጥታ ችግሮች ሲስተዋሉባት እንደነበር የቤጂንግ ሰዎች ያነሳሉ፡፡ ይህንን ተከትሎም አሁን ላይ ለግዛቲቱ አዲስ የጸጥታ ሕግ መውጣቱን ነው ቻይና ያስታወቀችው፡፡ ይሄንንም ሕግ በምክር ቤቷ ማጽደቋ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ ሕጉ ሆንግ ኮንግን ከቻይና የመገንጠል ሀሳብን፣ የሀገር ክህደትንና ሽብርተኝነትን ለመከላከልና ለማውገዝ ያለመ ነው ተብሏል፡፡ ከዚህ ባለፈም በሆንግ ኮንግ ጉዳይ የውጭ ጣልቃ ገብነትን ለመመከትም ያለመ ነው፡፡
የንብረት፣ የኮንትራት፣ የግለሰብ መብቶችን፣ ጋብቻና ቤተሰብ፣ ውርስና የፍትሐ ብሔር ተጠያቂነትን የሚመለከቱ ጉዳዮችን የያዘው ይህ አዲስ የጸጥታ ሕግ ታዲያ ከአሜሪካ እና የተለያዩ አጋሮቿ ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡
አሜሪካ የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት የሆንግ ኮንግን የጸጥታ ሕግ በተመለከተ አስቸኳይ ስብሰባ እንዲጠራና አጀንዳ እንዲያዝላት በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ማይክ ፖምፒዮ በኩል መጠየቋ ይታወሳል፡፡ ከዋሽንግተን በተጨማሪም ብሪታኒያ፣ካናዳ እና አውስትራሊያ አውግዘዋል፡፡
ከሳምንታት በፊት ሩሲያ የቻይናና የሆንግ ኮንግ ጉዳይ የውስጥ ጉዳይ ነው በሚል ድጋፏን ለቤጂንግ መስጠቷ ይታወሳል፡፡ ይህም ጉዳዩን ምዕራብና ምስራቅ ወደሚል ጎራ ያመራ ይመስላል፡፡