የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ ለስራ ጉብኝት ዛሬ አቡ ዳቢ ገቡ
የጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዙ አቤ በአገራቸውና በመካከለኛው ምስራቅ ጉዳዮች ላይ ለመምከር አቡ ዳቢ የገቡ ሲሆን ከአቡ ዳቢ ልዑል እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ ጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ አዛዥ ሼክ መሀመድ ቢን ዘይድ አል ነህያን ጋር ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በውይይታቸውም ጃፓን የጦር መርከቦቿን ወደ ቀጣናው ለመላክ ጀምራው የነበረውን ጉዳይ በተመለከተ እንደሚነጋሩ ተገልጿል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ በአቡዳቢ ጉብኝት ላይ ካሉት የኢንዶኔዥያ ፕሬዝዳንት ጆኮ ዊዶዶ ጋርም ተገናኝተው ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ጃፓንና መካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ጠንካራ የንግድ ትስስር እንዳላቸው የሃገሪቱ የኢኮኖሚ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል፡፡
ጃፓን 90 በመቶ የሚሆነውን ነዳጃ የምታገኘው ከመካከለኛው ምስራቅ ሲሆን 80 በመቶ የሚሆነው ደግሞ በዋነኛው የነዳጅ ማስተላለፊያ በሆርሙዝ ወደ ጃፓን የሚተላለፍ ነው፡፡
የጉብኝታቸው ዓላማም በሆርሙዝ አቅራቢያ ያለው የጸጥታና የደህንነት ሁኔታ ስጋት እንዳይገባው ለመነጋገር ነው ተብሏል፡፡