ማድሪድ ከፍተኛ ገቢ በማስገባት የሶስትዮሽ ዋንጫ ያሳካውን ሲቲ በለጠ
የስፔኑ ክለብ በ2022/23 የውድድር አመት 831 ሚሊየን ዩሮ ገቢ ማግኘቱ ተነግሯል
ማንቸስተር ሲቲ፣ ፒኤስጂ፣ ባርሴሎና እና ማንቸስተር ዩናይትድ እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል
ሪያል ማድሪድ የሶስትዮሽ ዋንጫ ያሳካውን ማንቸስተር ሲቲን በመብለጥ ከእግርኳስ ከፍተኛውን ገቢ የሚያስገባ የአለማችን ቀዳሚው ክለብ ሆኗል።
ደሎይት የተሰኘው ተቋም ባወጣው መረጃ መሰረት የስፔኑ ክለብ በ2022/23 የውድድር አመት ክብረወሰን የሆነ የ831 ሚሊየን ዩሮ ገቢ አስገብቷል።
በውድድር አመቱ የሻምፒዮንስ ሊግ፣ ፕሪሚየር ሊግ እና ኤፍኤ ካፕ ያሳካው የእንግሊዙ ማንቸስተር ሲቲ ደግሞ 826 ሚሊየን ዩሮ በማስገባት ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።
ማድሪድ በሻምፒዮንስ ሊግ ግማሽ ፍጻሜ በሲቲ ተሸንፎ በላሊጋውም ባርሴሎናን ተከትሎ ሁለተኛ ሆኖ ቢያጠናቅቅም የኮፓ ዴላሪ፣ የአውሮፓ ሱፐር ካፕ እና የፊፋ የአለም ዋንጫን ማንሳቱ ይታወሳል።
በዚህም ከ2017/18 የውድድር አመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲቲን በመብለጥ ከፍተኛ ገቢ ያስገባ ክለብ መሆን መቻሉ ተመላክቷል።
ከፍተኛ ገቢ ያስገቡት 20 ክለቦች ገቢ ካለፈው የውድድር አመት በ14 በመቶ አድጎ 10 ነጥብ 5 ቢሊየን ዩሮ መድረሱንም ነው የደሎይት መረጃን ጠቅሶ ቢቢሲ ያስነበበው።
ጨዋታዎችን በቴሌቪዥን በማስተላለፍ ክለቦች የ4 ነጥብ 2 ቢሊየን ዩሮ ገቢ ማግኘታቸውንና ይህም ከ2021/222 የውድድር አመት የ5 በመቶ እድገት ማሳየቱም ተገልጿል።
የፈረንሳዩ ፓሪስ ሴንት ጀርሜን፣ ባርሴሎና እና ማንቸስተር ዩናይትድ ከፍተኛ ገቢ በማስገባት እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።
የጀርመኑ ባየርሙኑክ በ744 ሚሊየን ዩሮ ስድስተኛ ደረጃ የያዘ ሲሆን፥ በ2021/22 የውድድር አመት ሶስተኛ ደረጃን ይዞ የነበረው ሊቨርፑል ወደ ሰባተኛ ዝቅ ብሏል።
ቶተንሃም፣ ቼልሲ እና አርሰናል ከስምንት እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ መያዛቸውንም ነው ደሎይት ይፋ ያደረገው።
ሌስተር ሲቲ፣ ሊድስ ዩናይትድ እና ኤቨርተን ከምርጥ 20 ዝርዝሩ ውጭ ሆነዋል።
በአለማችን ከፍተኛ ገቢ በሚያስገቡ 20 የእግርኳስ ክለቦች ዝርዝር ውስጥ ባለፉት ሁለት አመታት በጥቂቱ 10 ክለቦችን ያስመዘገበው የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊጉ በ2022/23 የውድድር አመት ስምንት ክለቦችን ብቻ አስመዝግቧል።
ኒውካስትል በ287 ሚሊየን ዩሮ፤ ዌስትሃም ደግሞ በ275 ሚሊየን ዩሮ 17ኛ እና 18ኛ ደረጃን ይዘዋል።
በደሎይት ከፍተኛ ገቢ ያስገቡ 20 የእግርኳስ ክለቦች ዝርዝር ውስጥ ገቢያቸው የቀነሰው ዌስትሃም፣ ሊቨርፑልና አትሌቲኮ ማድሪድ ብቻ ናቸው።