19ኛው የክለቦች የአለም ዋንጫ በሞሮኮ አስተናጋጅነት ተካሂዷል
የስፔኑ ክለብ ሪያል ማድሪድ የ19ኛው የክለቦች የአለም ዋንጫ ሻምፒዮን ሆኗል።
ማድሪድ የሳኡዲውን አል ሂላል ክለብ 5 ለ 3 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ነው አምስተኛውን የክለቦች የአለም ዋንጫ ወደ ማድሪድ የወሰደው።
በልኡል አብደላህ ስታዲየም በተደረገው የፍጻሜ ፍልሚያ ስምንት ጎሎት ተስተናግደዋል።
ፍሬድሪኮ ቫልቨርዴ እና ቪንሺየስ ጁኒየር ሁለት ሁለት እንዲሁም ካሪም ቤንዜማ አንድ ጎል ለሎስ ብላንኮስ (ነጫጮቹ) አስቆጥረዋል።
ለአል ሂላል ደግሞ ሙሳ ማሬጋ በ26ኛው፤ ሉቺያኖ ቬቶ ደግሞ በ63 እና 79ኛው ደቂቃ ጎሎቹን ማስቆጠር ችለዋል።
በ13ኛው ደቂቃ በቪንሺየስ ጁኒየር ጎል ጅማሮውን ያደረገው የፍጻሜ ጨዋታ በበርካታ ጎል የታጀበ መሆኑ በልኡል አብደላህ ስታዲየም ለታደሙ ደጋፊዎች እና በቀጥታ ለተመለከቱትም ተዝናኖትን የፈጠረ ሆኗል።
ሪያል ማድሪድ ትናንት ምሽት ያነሳው የክለቦች የአለም ዋንጫ ውድድሩ ከተጀመረበት ከፈረንጆቹ 2000 ወዲህ አምስተኛው ነው።
ክለቡ የአውሮፓና የደቡብ አሜሪካ ሻምፒዮን ክለቦች የሚያደርጉትን የዋንጫ ፍልሚያ ሶስት ጊዜ ማንሳቱ አይዘነጋም።የትናንቱ ድልም ማድሪድ በአለማቀፍ ውድድሮች ያነሳውን ዋንጫ ስምንት አድርሶታል።
ኤሲ ሚላን እና ባየር ሙኒክ አራት አራት ዋንጫዎችን በማንሳት ማድሪድን ይከተላሉ።
“ሪያል ማድሪድ ለስምንተኛ ጊዜ የአለም ሻምፒዮን በመሆኑ በጣም ደስተኛ ነኝ” ብለዋል የክለቡ አሰልጣኝ ካርሎ አንቸሎቴ።
ሞሮኮ ባስተናገደችው የአለም የክለቦች ዋንጫ ማድሪድ የግብጹን አል አህሊ 4 ለ 1 በመርታት ለፍጻሜ መድረሱ የሚታወስ ነው።
የሳኡዲ አረቢያው አል ሂላል ደግሞ የብራዚሉ ፍላሚንጎ በማሸነፍ ለመጀመሪያ ጊዜ ለፍጻሜ የደረሰ የሳኡዲ ክለብ ሆኗል።
የአለም የክለቦች ዋንጫ በአህጉራዊ የክለቦች የዋንጫ ፍልሚያዎች አሸናፊ የሆኑ ሰባት ክለቦች የሚሳተፉበት ውድድር ነው።
የአለም የእግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) ይህንኑ ውድድር ከ2025 ጀምሮ በየአራት አመቱ በ32 ክለቦች መካከል እንዲካሄድ እቅድ መያዙን ማርካ አስነብቧል።