ኢትዮጵያ በ2019 ያስተናገደቻቸው ዋና ዋና ፖለቲካዊ ክስተቶች ምንድናቸው?
ሊጠናቀቅ በጣት የሚቆጠሩ ቀናት የቀሩት የአውሮፓውያኑ 2019 የኢትዮጵያ የፖለቲካ ዓለም ያልሰከኑ በርካታ ውጣ ውረዶችን ያሳለፈበት ዓመት ነው፡፡ ሀገሪቱ በአራቱም ማዕዘኗ በርካታ አስከፊም አስደሳችም ፖለቲካዊ ክስተቶችን በዓመቱ አስተናግዳለች፡፡ ከነዚህ ክስተቶች ዋና ዋናዎችን በጥቂቱ እንደሚከተለው እንቃኛለን፡፡
የሰኔ 15 የባህርዳር ጥቃት እና የከፍተኛ አመራሮች ግድያ
ይህ ክስተት ብዙሃኑን ኢትዮጵያዊ ለከፍተኛ ድንጋጤና ሃዘን የዳረገ ሆኖ አልፏል፡፡ ጥቃቱ ግምገማ ላይ በነበሩ የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ላይ የተፈጸመ ሲሆን የክልሉን ርዕሰ መስተዳድር የአምባቸው መኮንን (ዶ/ር)፣የአማካሪያቸውየአቶ እዘዝ ዋሴ እና የአዴፓ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ምግባሩ ከበደን ህይወት ነጥቋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሃገሪቱ ጦር ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄነራል ሰዓረ መኮንን እና የጦር ኃይሎች የቀድሞው ባልደረባ ሜ/ጄነራል ገዛኢ አበራ የግድያ ዜና መሰማቱም ለብዘዎች በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ነበር፡፡
ጥቃቱ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ እንደሆነና ከባህርዳሩ ጥቃት ጀርባ የክልሉ አስተዳደርና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊ ብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ጽጌና ተባባሪዎቻቸው እንዳሉ መንግስት በወቅቱ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡
የባህርዳሩና የአዲስ አበባው ግድያ ግንኙነት እንዳላቸውም ነበር ሲገለጽ የሰነበተው፡፡
ሆኖም ብዙሃኑን ለድንጋጤ ዳርጎ ያለፈው የዚህ ግድያ ውስጠ ሚስጥር እስካሁን ለብዙዎች እንቆቅልሽ እንደሆነ ዘልቋል፡፡
የኦሮሚያ ቤተክህነት ፅህፈት ቤት ጥያቄና የቅዱስ ሲኖዶስ ምላሽ
ሊጠናቀቅ በተቃረበው የፈረንጆቹ 2019 አነጋጋሪ ከነበሩ ጉዳዮች መካከል አንዱ ነበር፡፡ ራሱን የኦሮሚያ ቤተክህነት አደራጅ ኮሚቴ ብሎ የሚጠራ አካልም ነበር ጥያቄውን ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ያቀረበው፡፡
ሆኖም ጥያቄው በብዙዎች በተለይም በምዕመናኑ ዘንድ ጥርጣሬንና ቁጣን ያጫረ ነበር፡፡ የቤተክርስቲያኒቷ የበላይ አካል ቅዱስ ሲኖዶሱም አውግዞታል፡፡
ጉዳዩን በተመለከተ ሊደረጉ ታስበው በነበሩ ሰልፎች ዙሪያ መንግስት ከየቤተክርስቲያኒቱ የበላይ አመራሮች ጋር ደጋግሞ መምከሩም የሚታወስ ነው፡፡
ብዙዎችን ያሰባሰበው የማህበረሰብ አንቂው (አክቲቪስት) የጃዋር መሃመድ የፌስቡክ ጥሪ
በጎላ የማህበረሰብ ማንቃት ስራውና በፖለቲካ ተጽዕኖ ፈጣሪነቱ የሚታወቀው ጃዋር በወርሃ ጥቅምት መባቻ በፌስቡክ የማህበረሰብ ትስስር ገጹ ያስነበበው ጥሪ ብዙ ዓይነት ምላሾችን ያስተናገደ ነበር፡፡
ጥሪው በመንግስት የተመደቡለት የግል ጠባቂዎች ምሽት ላይ እንዲነሱ መታዘዛቸውንና ስለጉዳዩ ለሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ቢያሳውቅም ምላሽ አለማግኘቱን የሚያሳውቅ ነበር፡፡
በጥሪውም ቄሮ የሚሰኙ የኦሮሞ ወጣቶች አዲስ አበባ በሚገኘው መኖሪያ ቤቱ አቅራቢያ ማልደው ተሰባስበው ነበር፡፡ የወጣቶቹ መሰባሰብ ጃዋርን ለመጠበቅ ቢሆንም በከተማዋ ውጥረትና የደህንነት ስጋትን ማንገሱ አልቀረም፡፡
ጥሪው አግባብ አለመሆኑን ዘግይቶም ቢሆን የፌዴራል ፖሊስ አስታውቋል፡፡ ሆኖም ክስተቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሩሲያ-አፍሪካ ትብብር መድረክ ለመሳተፍ እና ከግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ ጋር በህዳሴው ግድብ ጉዳይ ላይ ለመምከር ሞስኮ በነበሩበት ወቅት የተፈጠረ መሆኑ ከፍተኛ የደህንነት ስጋትና ውጥረትን በአዲስ አበባ እና በሌሎችም የሃገሪቱ አካባቢዎች እንዲነግስ አድርጎ ነበር፡፡
ውጥረቱን ተከትሎም በተከታዮቹ ቀናት ችግሮች ተፈጥረዋል፡፡
የብዙዎችን ህይወት የነጠቀው አመጽ
የጃዋርን ጥሪ ተከትሎ ድርጊቱን በማውገዝ በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞች የተካሄዱት የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ፈጥረዋል፡፡
ሰልፎቹን ተከትሎ በተቀሰቀሰ ግጭትም የሰው ህይወት አልፏል፤ ከፍተኛ የንብረት ውድመትና መቃጠልም ደርሷል፡፡ የሃይማኖት ተቋማትም ጭምር የአመጹ ሰለባ ነበሩ፡፡ በድርጊቱ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መድረሱን ያስታወቁ አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ጉዳዩን ወደ ህግ ይዘው ስለመሄዳቸው ሲነገርም ነበር፡፡
ጥቃቱ ሁላችንም ልንከላከለው ይገባል ያሉት ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ማዘናቸውን በገለጹበት ጽሁፍ ቀይ መስመር መጣሱን ጠቁመው ድርጊቱን ማውገዛቸውም የሚታወስ ነው፡፡
አመጹ የብሄርና የሃይማኖት መልክ እንዲይዝ ሙከራዎች ነበሩ ያለው መንግስትም የ86 ዜጎች ህይወት መጥፋቱን አስታውቋል፡፡
ዘግይተውም ቢሆን ባወጡት መግለጫ ድርጊቱን ያወገዙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድም በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች በመዘዋወር ከህብረተሰቡ፣ከአባገዳዎች እና ከወጣቶች ከተውጣጡ አካላት ጋር መክረዋል፡፡
የኢህአዴግ ውህደት
የኢህአዴግ መዋሃድ ጉዳይ ብዙ ሲያነጋግር የነበረ ነው፡፡ ድርጅቱ በ11ኛ ጉባዔው መዋሃድ እንዳለበት ወስኖ ነበር ቢባልም ውህደቱ በታሰበው ልክ መሄድ ሳይችል ቀርቶ እንደነበር የፓርቲው የአመራር አካላት ደጋግመው ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡
ወደ ስልጣን ከመጡበት ዕለት ማግስት ጀምሮ ስለ ኢህአዴግ “መበስበስ”ደጋግመው ሲናገሩ የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር)ም ጉባዔው ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ግንባሩን ለማዋሃድ ቀዳሚ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ ሲናገሩ ነበር፡፡ ተናግረውም አልቀሩም ውህደቱ ተፈጽሟል፡፡
ከህወሓት በስተቀር ሁሉም የግንባሩ አባልና አጋር ድርጅቶች ሃሳቡን አጽድቀውትም ውህደቱ ተፈጽሟል፡፡ ኢህአዴግም ስያሜውን ወደ ብልጽግና ቀይሯል፡፡ የግንባሩ ይፋዊ ውህደትም ህዳር 21 ቀን 2012 ዓ/ም በድርጅቶቹ መካከል በተካሄደ የፊርማ ስነ ስርዓት ተረጋግጧል፡፡
ሆኖም ውህደቱ ህወሓትን ጨምሮ ጊዜው አይደለም፤አሃዳዊነትንም ያመጣል ከሚሉ የፌዴራሊስት ሃይል ነን ባዮች ከፍተኛ ተቃውሞ ማስተናገዱ አልቀረም፡፡
የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ
የቆየ ጥያቄ እንደነበር የሚነገርለት የሲዳማ የክልልነት ጥያቄም በዚሁ ዓመት ምላሽ አግኝቷል፡፡
ለጥያቄው ምላሽ ይፈለግባቸው በነበሩ መንገዶች ሳቢያ ግን ችግሮች ማጋጠማቸው አልቀረም፡፡ ለዚህም በ2011 ዓ.ም. በ11ኛው ወር በ11ኛው ቀን ምላሽ ማግኘት አለብን በሚል በብሄሩ ወጣቶች (ኤጄቶ) ተቀምጦ የነበረው ቀነ ገደብ የፈጠረውን ችግር ማስታወስ ይቻላል፡፡ጥያቄውን አስመልክቶ በዕለቱ በሃዋሳ እና በሲዳማ ዞን የተካሄደውን ሰልፍ ተከትሎ በተፈጠረው ግርግር 25 ሰዎች መሞታቸው እና የከፋ የንብረት ውድመት መድረሱም በመንግስት አካላት ጭምር የተገለጸ ጉዳይ ነው፡፡
ለጥያቄው ምላሽ ለመስጠት ቅድመ ዝግጅት ሲያደርግ የቆየው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድም ህዳር 10 ቀን 2012 ዓ/ም በሃዋሳ ባካሄደው ህዝበ ውሳኔ ዞኑ 10ኛ የሃገሪቱ ክልል ሆኖ ለመዋቀር የሚያስችለውን የድምጽ ድጋፍ ማግኘቱን አስታውቋል፡፡
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ድርድር
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዲዛይን የተሰራው 16 የሀይል ማመንጫ ተርባይኖች እንዲኖሩት ታስቦ መሆኑ የሚታወስ ነው። እነዚህ 16 የሀይል ማመንጫ ተርባይኖች በተለያየ ጊዜ በተሰሩ የጥናት ማሻሻያዎች ከህዳሴው ግድብ የሚያመነጩት ሀይል 6450 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሀይል ይሆናል ተብሏል። ይሁንና አዲስ በተደረገ ክለሳ ከ16 የሀይል ማመንጫ ተርባይኖች ውስጥ ሁለቱ እንዲቀሩ ተወስኗል። ይሄም በግድቡ የማመንጨት አቅም ላይ ጉልህ ተጽዕና አይኖረውም በማለት መንግስት ቢገልጽም ህዝቡን ጥርጣሬ ውስጥ ማስገባቱ አልቀረም፡፡
ሌላው ከግድቡ ጋር የተያያዘው የዓመቱ ዋና ጉዳይ በግድቡ የውሀ ሙሌት እና አለቃቀቅ ላይ ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን በ2019 ሁለተኛ አጋማሽ ላይ ተከታታይ ድርድሮችን ማድረጋቸው ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሀገራቱ በዋሺንግተን ዲሲም የአሜሪካ እና የአለም ባንክ ታዛቢዎች በተገኙበት ድርድር ካደረጉ በኋላ በቀጣይነትም ታዛቢዎቹን በማሳተፍ ድርድራቸውን ቀጥለዋል፡፡
እስካሁን በነበራቸው ድርድር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መግባባት ችለዋል፡፡ ይሁንና በዚህ ወር መጨረሻ ላይ በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ድርድር ሀገራቱ የጋራ መግባባት ላይ የማይደርሱ ከሆነ ሌሎች ሀገራት በአሸማጋይነት ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡