በወታደሮች የታሰሩት የማሊ ፕሬዝዳንት ስልጣን መልቀቃቸውን ገለጹ
የማሊ ወታደሮች የሀገሪቱን ፕረዚደንት እና ጠቅላይ ሚኒስትር ጨምሮ ከፍተኛ ባለስልጣናትን ትናንት አስረዋል
የተመድ የጸጥታው ም/ቤት በማሊ ጉዳይ ላይ ዛሬ ለመምከር አስቸኳይ ስብሰባ ጠርቷል
በወታደሮች የታሰሩት የማሊ ፕሬዝዳንት ስልጣን መልቀቃቸውን ገለጹ
ትናንት ማክሰኞ ዕለት በመንግሥት ላይ ያመፁ የማሊ ወታደሮች የሀገሪቱን ፕረዚደንት ኢብራሂም ባውባካር ኬይታ እና ጠቅላይ ሚኒሰትር ባውባው ሲሴን ጨምሮ የሀገሪቱን ከፍተኛ ባለስልጣናት በቁጥጥር ስር አውለዋል።
በኮሎኔል ማሊክ ዲያው እና በጄኔራል ሳዲዮ ካማራ የተመሩት ወታደሮቹ በቅድሚያ የተቆጣጠሩት በዋና ከተማዋ ባማኮ አቅራቢያ የሚገኘውን የካቲ ካምፕ ነው። ካምፑን ከተቆጣጠሩ በኋላ ወደ ከተማው በመግባት ባለስልጣናቱን አስረዋል።
ፕረዚዳንት ኬይታ ከታሰሩ ከሰዓታት በኋላ ስልጣን መልቀቃቸውን ይፋ አድርገዋል።
ፕሬዚዳንቱ ስልጣን መልቀቃቸውን ባሳወቁበት ንግግራቸው የሀገሪቱ መንግስት እና ብሔራዊ ምክር ቤቱ እንደሚፈርሱ ገልጸዋል፡፡ የ 75 ዓመቱ ፕሬዝደንት ኬይታ በመሪነት ላይ በነበሩባቸው ዓመታት ህዝቡ ላደረገላቸው ድጋፍ ምስጋናም አቅርበዋል፡፡
በሀገቱ ቴሌቪዥን በተላለፈው ንግግራቸው ምንም አይነት የደም መፋሰስ እንዳይኖርም ፕሬዚደንቱ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ፕሬዚደንት ኬይታ በቁጥጥር ስር ከሚገኙበት ካቲ ካምፕ የመልቀቂያ ንግግር ሲያደርጉ
ድርጊቱ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት እንዳያስከትል የተሰጋ ቢሆንም ወታደሮቹ መንግሥቱን የመቆጣጠር ፍላጎት እንደሌላቸው መግለጻቸውን ፍራንስ 24 ዘግቧል።
በርካታ የሀገሪቱ ወታደሮች ፍጻሜ ያጣው ከጂሀዲስቶች (ኢስላማዊ አክራሪ ታጣቂዎች) ጋር በሚያደርጉት ውጊያ መሰላቸታቸው ተገልጿል። በሀገሪቱ ሙስናና ብልሹ አሰራር ነግሷል ያሉ የሀገሪቱ ዜጎችም ፕሬዚዳንቱ ስልጣን እንዲለቁ በመጠየቅ ከሁለት ወራት በላይ የተቃውሞ ሰልፍ አድርገዋል። ከዚህ ቀደም በአውሮፓውያኑ 2012 በወታደሮች በተካሔደ ተመሳሳይ የመንግስት ፍንቀላ ወቅት በተከሰተ ክፍተት ነበር ኢስላማዊ አክራሪ ታጣቂዎች የሀገሪቱን ሰሜናዊ ክፍል የተቆጣጠሩት፡፡ እነዚህ ታጣቂዎች አሁንም ድረስ ከማሊ በተጨማሪ ለአጎራባች ሀገራት ቡርኪና ፋሶ እና ኒጀርም ፈተና እንደሆኑ መዝለቃቸውን የሮይተርስ ዘገባ ያሳያል፡፡
ወታደሮቹ ትናንት የወሰዱትን እርምጃ የአፍሪካ ህብረት ፣ የተባበሩት መንግሥታት ፣ የአውሮፓ ህብረት እና ኢኮዋስን ጨምሮ በርካታ ድርጅቶች እና ሀገራት ያወገዙ ሲሆን የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ም/ቤት ዛሬ በሀገሪቱ ጉዳይ ላይ ለመምከር አስቸኳይ ስብሰባ ጠርቷል።
የሀገሪቱ ጦር አባላት ባለስልጣናት ከታሰሩ በኋላ በባማኮ ጎዳናዎች ሲዘዋወሩ
የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት የኢኮኖሚ ማህበር- ኢኮዋስ በሀገሪቱ የተከሰተውን ድርጊት በማውገዝ ትናንት ባወጣው መግለጫ ድርጊቱ በሀገሪቱ ያለውን የተወሳሰበ የማህበረ-ፖለቲካ ሁኔታ ይበልጥ የሚያባብስ መሆኑን ነው የገለጸው፡፡ ኢኮዋስ የማህበሩ አባል ሀገራት ከማሊ ጋር የሚያዋስናቸውን ድንበር እንዲዘጉም አሳስቧል፡፡
የአፍሪካ ህበረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት ባወጡት መግለጫ “የማሊ ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ባውባካር ኬይታ ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ባውባው ሲሴ እና ሌሎችም የማሊ መንግስት ባለስልጣናት በሀይል መታሰራቸውን በጽኑ አወግዛለሁ፣ በአስቸኳይ እንዲፈቱም እጠይቃለሁ” ብለዋል፡፡
ይሁን እንጂ በዋና ከተማዋ ባማኮ ነዋሪዎች በመሪዎቻቸው መታሰር ደስታቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡
የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ የወታደሮቹን ድርጊት ኮንነው በሀገሪቱ ሕገ መንግሥታዊ ስርዓት እንዲከበር ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት አባላት ፈረንሳይ እና ኒጀር ባቀረቡት ጥሪ መሰረት ም/ቤቱ ማሊ ጉዳይ ለመምከር ዛሬ በዝግ ስብሰባ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ወታደራዊ አመጹ የተነሳበት የካቲ ካምፕ በአውሮፓውያኑ 2012 ተመሳሳይ አመጽ ተቀስቅሶበት የወቅቱ ፕሬዝዳንት አማዱ ቶውማኒ ቱሬ ከስልጣን እንዲነሱ አድርጓል፡፡