በማሊ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ በመካሄድ ላይ መሆኑን ዘገባዎች አመለከቱ
በሙከራው ፕሬዝዳንት ኬይታን ጨምሮ ሚኒስትሮች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተሰምቷል
ከሙከራው ጋር በተያያዘ 14 ሰዎች ሞተዋል
በማሊ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ በመካሄድ ላይ መሆኑን ዘገባዎች አመለከቱ
በምዕራብ አፍሪካዊቷ ሃገር ማሊ ርዕሰ መዲና ባማኮ አቅራቢያ በሚገኘው የሃገሪቱ የጦር ኃይሎች ሰፈር የተኩስ እሩምታዎች እየተሰሙ መሆኑን የተለያዩ አህጉር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ብዙሃን መገናኛዎች ዘግበዋል፡፡
እሩምታው ከባማኮ 15 ኪሎ ሜትሮች በምትርቀውና ካቲ በተሰኘችው ከተማ ከሚገኘው ወታደራዊ ካምፕ መሰማቱን የአይን እማኞችን ዋቢ አድርጎ የዘገበው ሮይተርስ ሁኔታው ወደመፈንቅለ መንግስት ሊያመራ የሚችል አመጽ ሊሆን እንደሚችል ገልጿል፡፡
ማን በማን ላይ እንደሚተኩስ ግን ግልጽ የሆነ ነገር ባይኖርም ወታደሩ ብረት ማንሳቱንም ጠቁሟል፡፡
በማሊ ያሉ ጋዜጠኞች ነገሩኝ ያለው ኦል አፍሪካን በበኩሉ ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ቦባካር ኬይታን ጨምሮ አምስት ሚኒስትሮች ተይዘዋል ያለ ሲሆን የሃገሪቱ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ እና የፋይናንስ ሚኒስትሩ መታገታቸውን ዘግቧል፡፡
በማኮ ያለው የኖርዌይ ኤምባሲ አንታዘዝም ያሉ ወታደሮች ወደ ባማኮ በማቅናት ላይ መሆናቸውን መረጃዎች ደርሰውኛል ሲል ዜጎቹ እንዲጠነቀቁ ማሳሰቡንም ነው ሮይተርስ የዘገበው፡፡
ኮሎኔል ሳዲዮ ካማራ የወታደራዊ አመጹ መሪ ሊሆኑ እንደሚችሉም የጀርመኑ ዶቼቬሌ የመረጃ ምንጮች ነገሩኝ በሚል በእንግሊዘኛ ዘግቧል፡፡
ኮሎኔሉ ካማራ በካቲ የሚገኘው የወታደራዊ አካዳሚ የቀድሞ ኃላፊ ናቸው፡፡
ተካሂዷል በተባለው የተኩስ ልውውጥ የ14 ሰዎች ህይወት ማለፉንም ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅት አስታውቋል፡፡
ኬይታ ስልጣን እንዲለቁ የሚያጠይቁ የተቃውሞ ሰልፎች ከሰሞኑ በተደጋጋሚ ሲካሄዱ እንደነበር መረጃዎች አመልክተዋል፡፡
በማሊ እ.ኤ.አ በ2012 በተፈጸመ ተመሳሳይ አመጽ የአማዱ ቱማኒ ቱሬ መንግስት መገልበጡ የሚታወስ ነው፡፡