የታገደው ፍትሃዊ የክለቦች የገንዘብ አወጣጥ ህግን በመጣሱ ነው
ሲቲ ከሻምፒዮንስ ሊግ ውድድሮች ታገደ
ማንችስተር ሲቲ በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት በሚደረጉ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ውድድሮች እንዳይሳተፍ በአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ታገደ፡፡
እገዳው የክለቦች ፍትኃዊ የገንዘብ አወጣጥ ህግን (Financial Fair Play rules) በመጣስ ወጪውን ከገቢው ጋር ለማጣጣም በሚል በስፖንሰር መልክ የሚያገኘው ገቢ አጋኖ በማቅረቡ የተጣለ ሲሆን 33 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንዲቀጣም ተወስኖበታል፡፡
እ.ኤ.አ ከ2012 እስከ 2016 የነበረው የስፖንሰርሺፕ የገቢ ሪፖርት የተጋነነ ነው በሚል ምርመራዎች ጭምር ሲደረጉበት ነበር፡፡
በተለይም ታዋቂው የጀርመኑ የስፖርት ጋዜጣ ”ዴር ሽፒግል“ በ2018 በ‘ፉትቦል ሊክስ’ በኩል አፈትልከው የወጡ መረጃዎችን ተንተርሶ ያስነበባቸው ጉዳዩን የተመለከቱ ተከታታይ የምርመራ ዘገባዎች ምርመራው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ምክንያት ሆኗል፡፡
የማህበሩ የክለቦች ገንዘብ ተቆጣጣሪ አካልም ማስረጃዎችን በመመርመር ይህንኑ ስለማረጋገጡ አስታውቋል፡፡
ሲቲ በምርመራው ሂደት ለመተባበር ፍቃደኛ እንዳልነበርም ነው የገለጸው፡፡
ይህንኑ ታሳቢ በማድረግም ሲቲ የዘንድሮውን ጨምሮ በቀጣዩ ዓመት የሻምፒዮንስ ሊግ ውድድሮች እንዳይሳተፍ እና 33 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንዲቀጣ ወስኗል፡፡
ሲቲ የተባሉትን ጥሰቶች ስለመፈጸሙ አስተባብሏል፡፡ውሳኔው ምርመራው ከመጀመሩ በፊት የተላለፈ ነው በሚልም ነው ያስታወቀው፡፡
እንደ ጎል ስፖርት ዘገባ ከሆነ “በውሳኔው ባንገረምም አበሳጭቶናል” ባለበት መግለጫው ማህበሩ ”ራሱ ከሳሽ ራሱ ዳኛ ሆኖ አድሏዊ ውሳኔ“ ማሳለፉን አስታውቋል፡፡