ጋርዲዮላ እና አርቴታ ስለተጠባቂው የኢትሃድ ፍልሚያ ምን አሉ?
የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ የሚያነሳውን ክለብ ይወስናል የተባለው ጨዋታ ዛሬ ምሽት 4 ስአት ይደረጋል
የሁለቱም ቡድኖች አሰልጣኞች የኢትሃዱ ትንቅንቅ ዋንጫውን የሚያነሳውን ክለብ አይወስንም ብለዋል
የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግን በአምስት ነጥብ ልዩነት እየመራ ያለው አርሰናል በኢትሃድ ማንቸስተር ሲቲን ይገጥማል።
የ2003/04 ዋንጫን ለመጨረሻ ጊዜ ያነሱት መድፈኞቹ በኢትሃድ የሻምፒዮንስ ሊግ እና ኤፍ ኤ ካፕ ዋንጫን ለማንሳት ከተቃረበው ማንቸስተር ሲቲ ጋር የሚያደርጉት ፍልሚያ የዋንጫ ያህል ግምት ተሰጥቶታል።
በስድስት አመት ውስጥ አምስተኛውን የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ ለማንሳት የተሻለ ግምት የተሰጠው ሲቲ የዛሬውንና ቀሪ ሁለት ጨዋታዎቹን ካሸነፈ በሊጉ አናት ላይ ይቀመጣል።
ከ2016 እስከ 2019 የፔፕ ጋርዲዮላ ረዳት ሆኖ የሰራው ሚኬል አርቴታ፥ “ከባድ ፍልሚያ የምናደርግበት ምሽት ነው” ብሏል።
“ፕሪሚየር ሊጉን የማንሳት ፍላጎታቸውን ከጅማሮው አንስቶ ትልቅ ነው፤ ዋንጫውን ማንሳት ከፈለግን ደግሞ ሲቲን፣ ቼልሲ እና ቶተንሃምን ማሸነፍ ግዴታችን ነው” የሚል አስተያየቱንም ሰጥቷል።
በሁሉም ውድድሮች ባለፉት 13 ጨዋታዎች በ12ቱ ያሸነፈው ማንቸስተር ሲቲ አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ በበኩላቸው፥ “ከአርሰናል የመጀመሪያ ዙር ውጤት አንጻር ከዚህ እንደርሳለን ብለን አልጠበቅንም፤ ከዋነኛው ተቀናቃኛችን የምናገኘው ነጥብ እጅግ ወሳኝ ነው” ብለዋል።
የሁለቱም ቡድኖች አሰልጣኞች የኢትሃዱ ትንቅንቅ ዋንጫውን የሚያነሳውን ክለብ አይወስንም ቢሉም የቀደሙ ታሪኮች ግን ይህን አያሳዩም።
የዛሬው ጨዋታ ክለቦች ሊጉን በ5 ወይንም ከዚያ በታች እየመሩ በ33ኛውና ከዚያ በኋላ ባሉ ሳምንት ከተከታያቸው ጋር የሚያደርጉት 9ኛው ጨዋታ ነው።
በፕሪሚየር ሊጉ ታሪክ እየመራ በቼልሲ 2 ለ 1 ተሸንፎ ዋንጫ ያነሳው ማንቸስተር ዩናይትድ ነው፤ በ2008 በስር አሌክስ ፈርጉሰን።
በ2014ም መሪው ሊቨርፑል በቼልሲ 2 ለ 0 ቢሸነፍም ዋንጫውን ያነሳው ማንቸስተር ሲቲ እንደነበር ይታወሳል።
ዛሬ በኢትሃድ አርሰናል ከተሸነፈ ዋንጫ የማንሳት እድሉ በጣም ዝቅተኛ መሆኑን አሃዞችን የሚያጣቅሱ የስፖርት ተንታኞች ያነሳሉ።
የእርሶስ ግምት ምንድን ነው?