ስፔናዊው የአርሰናል አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ በቡድኑ ወቅታዊ አቋም ደስተኛ አለመሆኑ ገለጸ
መድፈኞቹ ከስፖርቲንግ ጋር በነበረው የዩሮፓ ሊግ ጨዋታ ደካማ አቋም አሳይተዋል
አርቴታ አርሰናል ከአውሮፓ ትላልቅ ቡድኖች ጋር ለመፎካከር መሻሻል አለበት ብሏል
ስፔናዊው የአርሰናል አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ በቡድኑ ወቅታዊ አቋም ደስተኛ አለመሆኑ ገለጸ
አሰልጣኙ ይህን ያለው አርሰናል በቅርቡ ከበርንማውዝ እና ከስፖርቲንግ ሊዝበን ጋር ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች አራት ግቦችን ማስተናገዱን ተከትሎ ነው፡፡
አርሰናል ትናንት ከስፖርቲንግ ጋር ባደረገው የዩሮፓ ሊግ ጨዋታ 2 ለ 2 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይቷል፡፡
ጨዋታውን ተከትሎ አስተያየቱን ለስካይ ስፖርት የሰጠው ሚኬል አርቴታ፤ የአርሰናል ተጨዋቾች ባሳዩት ብቃት ደስተኛ አለመሆኑ ተናግሯል፡፡
አርሰናል ከስፖርቲንግ ጋር በነበረው ጨዋታ በተለይም ተከላካይ ክፍሉ ደካማ ነበር ያለው አርቴታ፤ ከአውሮፓ ትላልቅ ቡድኖች ጋር ለመፎካከር ሁለንተናዊ መሻሻል የግድ መሆኑም አንስተዋል፡፡
በተጨማሪም አርሰናል ጋብሪኤል ጀሱስን ኳታር የአለም ዋንጫ ላይ በደረሰበት የጉልበት ጉዳት ምክንያት እስካሁን ሙሉ ብቃቱ አለመመለሱ እንደሁም አንዳንድ ቁልፍ ተጫዋቾች በሌሉበት ቡድኑ የተለመደው “የማጥቃት ጥምረት” ማጣቱን ተናግሯል አሰልጣኝ አርቴታ፡፡
በትናንቱ ጨዋታ በርካታ ለውጦች አድርጎ ሊሳካለት ያልቻለው አርቴታ፤ ከስፖርቲንግ ሊዝበን ጋር መጋቢት 16 በኤምሬትስ በሚደረገው የመልስ ጨዋታ ለውጥ ማሳየት ይጠበቅብናልም ነው ብለዋል፡፡
መድፈኞቹ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ማንቸስተር ሲቲ በአምስት ነጥብ ልዩነት በመምራት የፕሪምየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ በመምራት ላይ መሆናቸው ይታወቃል፡፡
እሁድ እለት ወደ ፉልሃም በመጓዝ በሚደርጉት ጨዋታ በጉጉት ሲጠበቅ ነበረው ገብርኤል ጀሱስ እንደሚሰለፍም ይጠበቃል፡፡