2019 ኢትዮጵያውያን በዓለማቀፍ መድረኮች የገነኑበት ዓመት ነው፡፡
በ2019 ዓለማቀፍ እውቅናና ሽልማት ያገኙ ኢትዮጵያውያን
በተጠናቀቀው 2019 ኢትዮጵያውያን በዓለም አቀፍ መድረኮች ስማቸው የናኘበት ዓመት ነው፡፡ በዚሁ ዓመት የሀገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር እና ፕሬዝዳንት ጨምሮ በርካታ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ዘርፎች በግለሰብም በቡድንም ደረጃ የተለያዩ ዓለማቀፍ ሽልማቶችንና እውቅናዎችን አግኝተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር)
100ኛውን የኖቤል የሰላም ሽልማት ያሸነፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ህዳር 30 ቀን 2012 ዓ.ም. በኖርዌይ አስሎ ሽልማታቸውን በደማቅ ስነስርዓት ተቀብለዋል፡፡ 900,000 የአሜሪካ ዶላርም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሽልማት አካል ነው፡፡
ሽልማቱን ተቀብለው ሲመለሱ “ኮሚቴው ያወቀውን ቢሸልምም ሽልማቱ ለሁላችንም የተሰጠ ነው ”ያሉት ዐቢይ (ዶ/ር) ፣አጋጣሚውን እንደ ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ሌሎች ችግሮችን ለመፍታት በመነሻነት ልንወስደው ይገባል ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አያይዘውም ኢትዮጵያ ውስጥ ትውልድ የሚበላ ሾተላይ አለ ያሉ ሲሆን ወደ መሰላል የሚወጡትን የሚበላውን ይህን ሾተላይ በማከም መደገፉ ለሁሉም እንደሚበጅ ነው የተናገሩት፡፡ መሰላል የሚወጡትን ጎትቶ ከማውረድ ይልቅ ከጫፍ እንዲደርሱ ልንደግፍ ይገባልም ብለዋል፡፡
ብዙዎች የተከታተሉት የሽልማት ስነስርዓቱ የኢትዮጵያና የኤርትራን ብሎም የቀጣናውን ገጽታ በመቀየር ረገድ የጎላ አበርክቶ ያለው በመሆኑ አጋጣሚውን በመጠቀም በተባበረ ክንድ ወደ ብልጽግና ልንሸጋገርበት ይገባል ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ፕሬዝደንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ
ፕሬዝደንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ ፎርብስ መጽሔት ለ2019 ዓ.ም. ከመረጣቸው 100 ተፅዕኖ ፈጣሪ ሴቶች መካከል አንዷ ሆነው ተመረጠዋል፡፡ በ2018 ጥቅምት ወር ላይ የኢትዮጵያ የመጀመሪያ ሴት ፕሬዝዳንት ሆነው የተሸሙት ሣህለ ወርቅ በአፍሪካ በስልጣን ላይ የሚገኙ ብቸኛዋ ርዕሰ ብሄር ናቸው፡፡ የእሳቸው በፕሬዝዳንትነት መሾም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ሴቶችን በብዛት ወደ ኃላፊነት በማምጣት የሚያከናውኗቸው የሪፎርም ተግባራት አካል እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡ፕሬዝዳንቷ በተባበሩት መንግስታትም ኢትዮጵያን ወክለው ለረዥም ዓመታት አገልግለዋል፡፡
ፍሬወይኒ መብራህቱ
ኢትዮጵያዊቷ ፍሬወይኒ መብራህቱ የ 2019 የ ሲኤንኤን ጀግና በሚል የክብር ሽልማት ተበርክቶላታል፡፡ ለሽልማት ያበቃት ደግሞ የወር አበባ ንፅህና መጠበቂያ ሞዴስ ለታዳጊ ኢትዮጵያውያን ልጃገረዶች እና ሴቶች በሀገር ውስጥ አምርታ ማቅረቧ ነው፡፡የ54 ዓመቷ ፍሬወይኒ በአሜሪካ የኬሚካል ኢንጂነሪንግ ትምህርት የተከታተለች ሲሆን፣ እንደ አውሮፓ አቆጣጠር ከ 2005 ጀምሮ ታጥቦ በድጋሚ ጥቅም ላይ መዋል የሚችል ታዳሽ ሞዴስ እያመረተች የበርካታ ኢትዮጵያውያን ሴቶችን ችግር ማቃለል ችላለች፡፡
ህዳር 28 ቀን 2012 ዓ.ም. እሁድ ምሽት የክብር ሽልማቷን በተረከበችበት ወቅት “ምን እንደምል እንኳን አላውቅም፡፡ ትልቅ ክብር ተሰምቶኛል፤ ይህ ሽልማት የመላው ሴቶች ነው፡፡” ስትል ወ/ሮ ፍሬወይኒ መብራህቱ በዝግጅቱ ታዳሚያን ፊት ተናግራለች፡፡ወ/ሮ ፍሬወይኒ ባጠቃላይ የ110 ሺ ዶላር ሽልማት አሸንፋለች፡፡ ሽልማቱ ሲ.ኤን.ኤን. አለምን የተሸለ ስፍራ ለማድረግ ለሚተጉ ግለሰቦች በየአመቱ የሚያበረክተው ነው፡፡
ተወልደ ገብረማርያም
ካፓ (CAPA) የተሰኘ ዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ማእከል ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም እውቅና አበርክቶላቸዋል፡፡
”የዓመቱ የአየር መንገዶች ዋና ስራ አስፈጻሚ“ የተሰኘው እውቅና ለአቶ ተወልደ የተሰጣቸው ለአየር መንገዱ እድገት ለተጫወቱት የላቀ የአመራርነት ሚና መሆኑን ማዕከሉ አስታውቋል፡፡ በዚህም ለ አቪዬሽን ኢንዱስትሪው እድገት አቶ ተወልደ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳደረጉ በማዕከሉ ተመስክሮላቸዋል፡፡ የሽልማት ስነ ስርዓቱ የተካሄደው ህዳር 25 ቀን 2012 ዓ.ም. በማልታ መሆኑን ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሚያስተናግዳቸው መንገደኞች ቁጥር፣ በገቢ መጠን እና የተለያዩ ዘርፎች ፈጣን እድገት እያስመዘገቡ ከሚገኙ ቀዳሚ አየር መንገዶች ተርታ የሚሰለፍ ሲሆን ለዚህ ስኬቱም የዋና ስራ አስፈጻሚው የአመራር ብቃት ዋና ምክኒያት እንደሆነ ይታመናል፡፡
ደራርቱ ቱሉ
ኢትዮጵያ በአትሌቲክሱ መስክ ከውጤት ባሻገር 2019 ዓ.ም. ታላላቅ አትሌቶቿ እና የአትሌቲክሱ ፈርጦች እውቅና ያገኙበትም ነው፡፡ የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌደሬሽን የባርሴሎና ኦሎምፒክ ንግስቷን ደራርቱ ቱሉን ያኔ በውድድር አሁን በስፖርት አመራርነት እየተወጣች ላለችው በጎ ሚና የዓመቱ ምርጥ ሴት ብሎ ሸልሟታል፡፡
ከላይ ከተጠቀሱት ኢትዮጵያውያን በተጨማሪ ሌሎች የተለያዩ ኢትዮጵያውያንም በተለያዩ ዘርፎች እውቅና ተችሯቸዋል፡፡ ለአብነትም የአፍሪካ ስፖርት ፌደሬሽን ደግሞ በአትሌቲክስ እና የአመራር ብቃቱ ኃይሌ ገብረስላሴን ሸልሞታል፡፡ ድምጻዊ አብርሀም በላይነህ (ሻላዬ) ለ6ኛ ግዜ በተካሄደው የAfrima Award "እቴ አባይ" በተሰኘው ነጠላ ዜማው በአፍሪካ ባህላዊ ሙዚቃ ዘርፍ አሸናፊ ሆኗል። ናይጄሪያ ባስተናገደችው የአፍሪካ የባህል ሙዚቃ ፌስቲቫል ውድድር የደቡብ ባህል ሙዚቀኞች ቡድን ኢትዮጵያን በመወከል ያሸነፈውም በአውሮፓውያኑ 2019 የመጨረሻ ወር ላይ ነው።