መሀመድ ቢን ዘይድ ለሰላም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ምርጥ የአረብ መሪ ተብለው ተመረጡ፡፡
ሼክ መሀመድ ቢን ዘይድ አል ነህያን ፣ የአቡ ዳቢ ልዑል እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ ጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ አዛዥ ፣ እ.ኤ.አ. በ 2019 ለሰላም እና አለማቀፍ ትብብር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ምርጥ የአረብ መሪ ተብለው ነው የተመረጡት፡፡
በሩሲያ አለማቀፍ ቴሌቪዥን-RT በተሰበሰበ ድምጽ፣ ከሳዑዲው ልዑል መሀመድ ቢን ሰልማን እና ከተለያዩ የዓረብ ሀገራት መሪዎች ጋር ተወዳድረው ነው ልዑሉ እውቅና የተቸራቸው፡፡
መሀመድ ቢን ዘይድ በተጠናቀቀው የአውሮፓውያኑ ዓመት ጽንፈኝነትንና አክራሪነትን ለመከላከልም ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል ተብሏል፡፡
እኚህ የአቡ ዳቢ ልዑል የኢትዮጵያና ኤርትራ እንዲሁም የፓኪስታንና ህንድ መሪዎችን አቀራርበው ማነጋገራቸው ይታወቃል፡፡ ኢትዮጵያና ኤርትራ የቆየ ጸባቸውን በመተው አሁን ለደረሱበት ሰላማዊ ግንኙነት እንዲበቁ ሼክ መሀመድ የራሳቸውን አሻራ አሳርፈዋል፡፡
ምንም እንኳን ህንድና ፓኪስታን ከካሽሚር ግዛት ጋር በተያያዘ ለረዥም ዓመታት የዘለቁበት ውዝግብ እዚህ ግባ የሚባል ለውጥ ባያመጣም ሁለቱን ሀገራት በማደራደር ሰላም ለማስፈንም ሼክ መሀመድ ቢን ዘይድ የተቻላቸውን ጥረት አድርገዋል፡፡
ትብብር እናአብሮ መስራትን በማበራታታት ረገድ ከተለያዩ የዓለም ሀገራት መሪዎች ጋር በነበራቸው ቆይታ ከፍተኛ ሚና እንደተወጡም ይነገርላቸዋል፡፡
ልዑሉ በዓለማቀፍ እና ቀጣናዊ የሰላምና ትብብር ጉዳዮች በተጫወቱት ሚና ሀገራቸው በዓለም በበጎ ተጽእኖ ፈጣሪነት እንድትታወቅ አድርገዋል ነው የተባለው፡፡