በሀገሪቱ የፖሊስን ጭካኔያዊ እርምጃ በመቃወም በተጀመረው ሁከት በትንሹ 69 ሰዎች ተገድለዋል
በናይጄሪያ የተፈጠረውን ሁከት ለመቆጣጠር አጠቃላይ የሀገሪቱ ፖሊስ እንዲሰማራ ታዘዘ
የፖሊስን የጭካኔ እርምጃ በመቃወም ተጀምሮ ወደ ከፍተኛ የጎዳና ላይ ነውጥ እና ዝርፊያ ለመቆጣጠር የናይጄሪያ ፖሊስ አዛዥ አጠቃላይ የፖሊስ ኃይሉ ለግዳጅ እንዲሰማራ አዝዘዋል፡፡
በአፍሪካ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ባለቤት በሆነችው ናይጄሪያ የአሁነ የጎዳና ላይ ነውጥ ከ20 ዓመታት በኋላ ከፍተኛው ነው፡፡
እ.ኤ.አ. ከ2015 ጀምሮ ምርጫ አሸንፈው ናይጄሪያን በፕሬዝዳንትነት የሚመሩት የቀድሞው የሀገሪቱ ጦር መሪ ሞሃመዱ ቡሃሪ በስልጣን ዘመናቸው ከፍተኛው የፖለቲካ ቀውስ እንደገጠማቸውም ነው የሮይተርስ ዘገባ የሚያመለክተው፡፡ ችግሩን ለመቆጣጠር በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሠዓት እላፊ ቢታወጅም ለውጥ ማምጣት ግን አልተቻለም፡፡
ህዝባዊ አመጹ ይበልጥ ተቀጣጥሎ ነውጡ የበረታው ደግሞ ባለፈው ማክሰኞ በሀገሪቱ የንግድ ማዕከል ሌጎስ የተቃውሞ ሰልፈኞች ከተገደሉ በኋላ ነው፡፡ በእለቱ የጸጥታ ኃይሎች በወሰዱት እርምጃ በትንሹ 12 ሰዎች መገደላቸውን የአይን እማኞች እና አምኔስቲ ኢንተርናሽናል ገልጸዋል፡፡
ልዩ የጸረ ዝርፊያ ስኳድ የተሰኘው የፖሊስ ክንፍ ይፈጽማቸዋል የተባለውን የጠለፋ ፣ የአስገድዶ መድፈር እና በኃይል ንብረትን የመንጠቅ ወንጀሎች በመቃወም ከ2 ሳምንት በፊት የጎዳና ላይ ነውጥ ከተጀመረ ወዲህ በትንሹ 69 ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል፡፡ ከሟቾቹ አብዛኛው የተቃውሞ ሰልፈኞች ቢሆኑም የጸጥታ አካላት ይገኙበታል ተብሏል፡፡ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በተለይም በደቡቡ የሀገሪቱ ክፍል በተቃውሞ ሰልፈኞች በርካታ ህንጻዎች ተጎድተዋል ፤ በርካታ የግል እና የመንግስት ንብረትም ተዘርፏል፡፡
በተለይም በክሮስ ሪቨር ግዛት ለአደጋ ጊዜ የተቀመጠ የምግብ ክምችት ጭምር የተዘረፈ ሲሆን ዝርፊያው ወደ ተለያዩ ተቋማትም በመዛመት የግዛቲቱ የሰላም እና የደህንነት ስጋት በመሆን ላይ እንደሚገኝ ባለሥልጣናት ገልጸዋል፡፡
ይህን ተከትሎ በሀገሪቱ እየተፈጸመ ያለውን አመጽ ፣ ዘረፋ እና የንብረት ውድመት ለማስቆም የናይጄሪያ ፖሊስ በሙሉ ኃይሉ እንዲሰማራ በፖሊስ አዛዡ ሞሃመድ አዳሙ ትናንት ጥቅምት 14 ቀን 2013 ዓ.ም ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡