በረራ ላይ የነበረ አውሮፕላንን አጋያለው በሚል የዛተው ግለሰብ የ10 አመት እስር ይጠብቀዋል ተባለ
የ45 አመቱ ጎልማሳ ከአውስትራሊያ ወደ ማሌዥያ በመብረር ላይ የነበረ ኤርባስ አውሮፕላን ተመልሶ እንዲያርፍ አስገድዷል
የግለሰቡ ጠበቃ ጎልማሳው የአዕምሮ ጤናው የተቃወሰ መሆኑን ገልፀዋል
ከአውስትራሊያ ወደ ማሌዥያ በመብረር ላይ የነበረ አውሮፕላን ላይ ጥቃት እንደሚሰነዝር የዛተው መንገደኛ በቁጥጥር ስር ውሏል።
ሞሀመድ አሪፍ የተባለው የካንቤራ ነዋሪ መነሻውን ሲድኒ መዳረሻውን ደግሞ ኳላላምፑር ባደረገውና የበረራ ቁጥሩ "ኤምኤች122" በሆነ አውሮፕላን ተሳፍሯል።
የ45 ከመቱ ጎልማሳ ጮክ ብሎ ፀሎት ሲያደርስ አንዳንዶች ስቀውበታል፤ ለሁላችንም መልካም ተመኝቶ ነው ያሉ በአጠገቡ የተቀመጡ ሰዎችም ነበሩ።
አብዛኞቹ ጉዟቸውን የሚያስተጓጉል ድንገተኛ ገጠመኝ ይከሰታል ብለው ግን አልጠበቁም።
በረራው ከተጀመረ ከአንድ ስአት ተኩል በኋላ ግን አሪፍ ድምፁን ከፍ አድርጎ ማውራትና ከመቀመጫው ተነስቶ መረበሽ ጀመረ ይላሉ ከጀርባው የተቀመጡ መንገደኞች።
ቦርሳውን በእጁ ይዞ ፈንጂ መያዙን ደጋግሞ መግለፁም መደናገጥ መፍጠሩንና አውሮፕላኑ ከተነሳ ከሶስት ስአት በኋላ ዳግም ወደ ሲድኒ ለመመለስ መገደዱን ኤቢሲ ኒውስ ዘግቧል።
የማሌዥያ አየር መንገድ አብራሪው የመንገደኞቹን ደህንነት ለመጠበቅ ወደ መነሻው ለመመለስ መወሰኑን አስታውቋል።
ኤርባስ330 አውሮፕላኑ ሲድኒ አለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ካረፈ በኋላም መንገደኞች ለመውረድ ሶስት ስአት መጠበቅ ግድ ብሏቸዋል።
"የአደጋ ጊዜ ተሽከርካሪዎች እና ፓሊሶች ሲከቡን እና በድረገፆች ላይ የቦምብ ጥቃት ሊደርስብን እንደሚችል ማንበባችን በጣም ረብሾን ነበር" ብለዋል አንድ መንገደኛ።
ፓሊስ ሞሀመድ አሪፍን በቁጥጥር ስር አውሎ በሰላም ከአውሮፕላን ሲወጡ ግን ስጋታቸው ሁሉ መሰረተ ቢስ እንደሆነ ተረጋግጧል።
አሪፍ ምንም አይነት ፈንጂ አለመያዙ የተገለፀ ሲሆን፥ በዛሬው እለትም ክስ ተመስርቶበታል።
ጎልማሳው እስከ 10 የሚደርስ እስራት እና 7 ሺህ 300 የአሜሪካ ዶላር ቅጣት ሊጣልበት እንደሚችልም ነው የተነገረው።
የግለሰቡ ጠበቃ ግን አሪፍ የአዕምሮ ጤና ችግር እንዳለበት እና የአውሮፕላን ጥቃት ዛቻውም ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው በሚል ተከራክረዋል።