ባሌ አስታዋሽ ምትኩን ሰጥቶኛል የምትለው እናት በምን ተአምር ህይወቱ ካለፈ ባሏ ልትወልድ እንደቻለች ትናገራለች
ከሶስት አመት በፊት በሞት ከተለያት ባሏ የመጀመሪያ ልጇን በቅርቡ መውለዷን የተናገረችው እናት መነጋገሪያ ሆኗለች።
የ34 አመቷ ስያን ጉድሴል ከፍቅረኛዋ ጃሰን ጋር በ2014 ነበር በፍቅር አጋር ማገናኛው ቲንደር የተዋወቁት።
ለአመታት የዘለቀው ወግም እያደገ ሄዶ በአካል ወደመገናኘትን ረጅም ጉዞን ወደማድረግ አደገ።
አውስትራሊያውያኑ ጥንዶች በየካቲት ወር 2017 ጉብኝት ላይ በነበሩበት ወቅት ግን አስደንጋጭ መርዶ ይሰማሉ።
ጃሰን በፍቅርን ክንፍ ላለላት ስያን የታገቢኛለሽ ጥያቄ አቅርቦ ይሁንታዋን ባገኘ በስድተኛው ቀን ለቀላል ህክምና ባመራበት ሆስፒታል ደረጃ 4 የጉበት ካንሰር እንዳለበት ተነገረው።
ለሁለት አመታት ህክምናውን ሲከታተል ቆይቶም ከሲያን ጋር በሆስፒታል ውስጥ በይፋ በተጋቡበት ምሽት ይህቺን አለም ይሰናበታል።
ህመሙ ለሞት እንደሚያበቃው አስቀድሞ የታመነበት በመሆኑም ጋብቻው ነፍሱን ለማስደሰት ብቻ የተካሄደ ነበር።
በሞት አፋፍ ላይ የነበረው ጃሰን ህይወቱን እያፈካችው ከነበረችው ሲያን ጋር መለያየቱ አይቀሬ መሆኑን ሲያውቅ ፍቅሯ ህያው ቢሆንም ህይወት ስለሚቀጥል ሌላ አግብታ እንድትኖር ይመክራት ያዘ።
ሲያን ግን “ሌላ አላገባም” በሚል አቋም ጸናች፤ እርሱን የሚያስታውስ አንድ ልጅ የምታገኝበትን መንገድም ታወጣ ታወርድ ጀመር።
ለሀኪሞች ስታማክርም የሚሞትበት ቀን እየተቆጠረለት ያለው ባሏ የዘር ፍሬ ቢወሰድ ለረጅም ጊዜ ሊቀመጥ እንደሚችልና በቤተሙከራ ጽንስ ሊፈጠር እንደሚችል ተነገራት።
እናም ጃሰን የካንሰር ህዋሳትን በጨረር ለመግደል ከሚደረገው ህክምና በፊት የዘር ፍሬው ተወስዶ በቀዝቃዛ ስፍራ ተቀመጠ።
ከዚያም የዘር ፍሬው ከሲያን እንቁላል ጋር በላቦራቶሪ ተዋህዶና ጽንስ ሆኖ በሰው ሰራሽ ማህጸን ወይም ሽል እንዲቆይ ተደረገ።
ይህ ጽንስም በቀዶ ህክምና ወደ ማሕጸኗ እንዲገባ ተደርጎ ከስድስት ወራት በኋላ በታህሳስ 2022 (ባሏ ህይወቱ ካለፈ ከሶስት አመት በኋላ) ማቲልዳ የተሰኘች ልጅ ወልዳለች ብሏል ዴይሊ ሜል በዘገባው።
“ማቲልዳ ያለጊዜዋ ተወልዳ ለ17 ሳምንት ሆስፒታል ውስጥ ያሳለፍኩት ከባድ ጊዜ ቢሆንም አሁን ጤነኛ ናት፤ ደግሞ ቁርጥ ጃሰንን ነው የምትመስለው” የምትለው ሲያን፥
ከ9 አመት በፊት በቲንደር ከተዋወቀችው፤ ከሶስት አመት በፊት ህይወቱ ካለፈ የቀድሞ ባሏ ልጅ መውለዷን የቅርቦቿ ሁሉ ማመን እንደቸገራቸው ትናገራለች።