ስኬታማ የስራ ፈጣሪ ለመሆን ምን እንድርግ?
ስራ ፈጣሪነት በበርካታ ፈተናዎች የተሞላና የማይቋረጥ ትጋትን ይጠይቃል
ስኬታማ የስራ ፈጣሪ ለመሆን አብዝተን የምንወደውን ሙያ መለየትና ግልጽ እቅድ ማውጣት ቀዳሚው ተግባር ነው
በዚህ ነገሮች በፍጥነት በሚለዋወጡበት አለም የስራ ፈጣሪነት ጉዳይ ከፍተኛ ትጋትን ይጠይቃል።
ስራ ፈጣሪ ለመሆን የሚተጉ ሰዎች የፈጠራ ነጻነትን እና ፈጠራቸው ይዞላቸው የሚመጣውን ጥቅም አስቀድመው ቢያስቡም የሚያልፉበት መንገድ ግን ፈታኝ ነው።
ስኬታማ ስራ ፈጣሪ ለመሆን በርካታ ፈተናዎችን ማለፍ፤ መውደቅ እና መነሳት እንዲሁም የማይቋረጥ ትጋት ማድረግን ይጠይቃል።
ከዚህ በታች የተዘረዘሩት 10 ነጥቦችም ስኬታማ የስራ ፈጣሪ ለመሆን የሚያግዙ ወሳኝ መንገዶች ናቸው።
1. የምንወደውን ሙያ እና ራዕያችን መለየት
የእያንዳንዱ ስኬታማ ስራ ፈጣሪ ታሪክን ብንመረምር የመጀምሪያ የስኬት መንገዱ የሚወደውን ነገር የመለየት እና በዚያ ዘርፍ መዳረሻ ራዕዩን የማወቁን ጉዳይ ከፊት እናገኘዋለን።
የራስን የተለየ ፍላጎት፣ ልዩ ችሎታ እና ልምድ ለይቶ ከስኬት የሚያደርስ ግልጽ እቅድ መንደፍ ይገባል። በሚገባ የተጻፈ ራዕይ የስኬት አመላካች ኮምፓስ ሆኖ ያገለግላል።
2. ራስን በእውቀት ማዳበር፤ ሁሌም መማር
በየእለቱ ለእውቀት እና አዳዲስ ፈጠራዎች መጠማት የስኬታማ የስራ ፈጣሪነት ሌላኛው ወሳኝ መንገድ ነው። መጽሃፍትን ማንበብ፣ ከሙያችን ጋር የተያያዙ ስልጠናዎችን መውሰድ፣ የስራ ፈጠራ አማካሪዎችን ማነጋገር እና አዳዲስ እውቀት እየገበዩ ከፈጣኑ አለም ጋር መቀራረብ ያስፈልጋል።
3. ከፈተናዎች መማርና መጽናት
በስራ ፈጠራ ውስጥ ለችግሮች እጅ የማይሰጥ ጠንካራ ጽናትን መገንባት ወሳኝ ነው። በእያንዳንዱ ጉዞ ውስጥ መውጣት መውረድ እንዳለ ማመንና ችግሮችን ለተሻለ ነገ መማሪያ እንጂ ተስፋ መቁረጫ አድርጎ አለመውሰድ ይገባል። ያስታውሱ እጅግ ውጤታማ ስራ ፈጣሪዎች በርካታ ፈተናዎችን በጽናት ተፋልመው ነው ከስኬት ጫፍ የደረሱት።
4. የተጠና የቢዝነስ እቅድ ማውጣት
የገበያ ጥናት ማድረግ፣ ዋናዋና የቢዝነሳችን መዳረሻዎች መለየት፣ ተፎካካሪዎቻችን ያላቸውን የተለየ አገልግሎትና ብቃት ማጥናትና የኛን የተለየ ውጤታማ መንገድ መዘርዘር ለቢዝነስ እቅዳችን ዋነኛ ግብአቶች ናቸው። የምንከውናቸውን ተግባራት በጊዜ ገደብ ለይቶ ማስፈር፣ ወጪና ገቢያችን ምን ያህል ሊሆን እንደሚችል የሚያሳይ እንዲሁም የገበያ ስትራቴጂ መንደፍም ወሳኝ ነው። ከላይ የጠቀስናቸውን ነጥቦች ያካተተ የቢዝነስ እቅድ ሌሎች ሰዎች አብረውን እንዲሰሩ ከመጋበዙም በላይ ከግባችን ለመድረስ እንደመሰላል ያገለግለናል።
5. ከሚመስሉንን ጋር መወዳጀትን ማጠናከር
በስራችን የሞራልና የእውቀት ድጋፍ የሚሰጡን ባለሙያዎች፣ አማካሪዎች እና ጓደኞች ማብዛት ወደ ስኬት ለመቅረብ ሌላኛው መንገድ ነው። ከስራ ፈጠራ ጋር በተያያዙ ሁነቶች መሳተፍና የስራ ማህበራትን መቀላቀል ከሙያችን ጋር ተቀራራቢ የሆኑና ድጋፍ ሊሰጡን የሚችሉ ሰዎችን ለማግኘትና ትስስር ለመፍጠር ይረዳናል። ይህ ትስስርም በጋራ ተቋም የመገንባት እና ሃብትን የማፍራትን በር ይከፍታል።
6. ኪሳራን ግምት ውስጥ ማስገባት
ስኬታማ ስራ ፈጣሪዎች ሊገጥማቸው የሚችለውን ኪሳራ ቀድመው ይገምታሉ፤ የሚገጥም ኪሳራም አስደንግጧቸው ወደኋላ ሲያስቀራቸው አልተስተዋለም። ከተለምዷዊው የምቾት ቀጠና አስቀድመው ለመውጣት ስለወሰኑ ከባድ ኪሳራ ቢገጥማቸው እንኳን አይሰበሩም። አንዳንዶቹ እንደውም ከደረሰባቸው ኪሳራ አንጻር ዳግም ይነሳሉ ተብለው ያልተጠበቁ ናቸው። ነገር ግን ሲጀምሩትም ኪሳራውን አስልተው ስለተዘጋጁበት ከግባቸው ደርሰዋል።
7. ደንበኛ ላይ ማተኮር
ስኬታማ የስራ ፈጣሪ ደንበኞቹንና ፍላጎታቸውን ጠንቅቆ ያውቃል፤ አስተያየታቸውን ያደምጣል። የደንበኞቹን እርካታ መጨመር ይዞት የሚመጣውን ገበያ ይረዳልና ሁሌም ከደንበኞቹ ጋር የቤተሰባዊ ያህል ቅርርብን ይፈጥራል። የተለየና አዳዲስ ፈጠራዎችን በማከል ደንበኞቹን ለማስደሰትም ያለማቋረጥ ይተጋል።
8. የጊዜና ሃብት አጠቃቀምን ማዘመን
ስራ ፈጣሪዎች ጊዜ እና ሃብታቸውን በአግባቡ ማስተዳደር የሚችሉበትን ስርአት ማበጀት አለባቸው። ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮችን መለየት እና ተጽዕኗቸው ከፍ ያሉ ጉዳዮች ላይ ማተኮርም ይኖርባቸዋል። ስራዎችን በፍጥነት እና በዝቅተኛ ወጪ ማጠናቀቅ የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን ሊጠቀሙ ይገባል።
9. ለአዳዲስ ፈጠራ ዝግጁ መሆን
የስራ ፈጠራው አለም በየጊዜው የሚለዋወጥ እንደመሆኑ ከሳይንስና ቴክኖሎጆ ፈጠራዎች ጋር ራስን ማወዳጀት ተገቢ ነው። ሌሎች ስራ ፈጣሪዎች የሚከተሏቸውን አዳዲስ ፈጠራዎች እና ቴክኖሎጂዎች በማጥናትም ከራሳችን የስራ ፈጠራ ጋር አብሮ የሚሄድ ለውጥ ማድረግ ያስፈልጋል። ሁሌም ለአዳዲስ ፈጠራ ዝግጁ መሆን ፉክክር በበዛበት አለም ውስጥ ወሳኝነቱ አያጠያይቅም።
10. ስኬትን ማክበር
በመጨረሻም በእያንዳንዱ የስኬት ምዕራፍ ውስጥ ውጤታማ ስራዎችን ለማስቀጠል ድሉን ማክበር ለዘላቂነቱ ወሳኝ ነው። በብዙ ፈተና ውስጥ የተገኘውን ውጤት መዘከር ለሌላ አዲስ ስኬት ስለሚያነቃ በመንገዳችን ውስጥ ድርሻ ከነበራቸው ጋር ጊዜ ማሳለፍና እውቅና መስጠት ይገባል።