ሩይ ፒንቶ የኤሳቤላ ዶሳንቶስን የሙስና ቅሌቶች እንዳጋለጠ አስታውቋል
በቅርቡ ከተጋለጡት የአንጎላ የሙስና ቅሌቶች ጀርባ እጁ እንዳለበት ፖርቹጋላዊው መረጃ በርባሪ ተናገረ
የ31 ዓመቱ ፖርቹጋላዊ የመረጃ በርባሪ (ሃከር) ሩይ ፒንቶ በቅርቡ አፈትልከው ከወጡት የአንጎላ የሙስና ቅሌቶች ጀርባ እጁ እንዳለበት በህገ ወጥ የመረጃ ብርበራና ዝርፊያ ተከሶ ለቀረበበት ፍርድ ዳኞች አስታውቋል፡፡
ሩይ ከሰሞኑ በአንጎላ መንግስት በሙስና ወንጀል የተከሰሱትን ቢሊዬነሯን ኤሳቤላ ዶሳንቶስን ያጋለጠው እሱ መሆኑንም ነው ለዳኞቹ የተናገረው፡፡
ቢሊዬነሯን የተመለከቱ ናቸው ያላቸውን መረጃዎች ያከማቸበትን ’ሃርድ ዲስክም’ ለፍርድ ቤቱ አስረክቧል፡፡
ኤሳቤላ የቀድሞው የአንጎላ ፕሬዝዳንት ጆዜ ኢድዋርዶ ዶሳንቶስ ልጅ ናቸው፡፡ ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም በህገወጥ መንገድ ከሃገሪቱ የማዕድን ተቋማት በሚመዘበር ገንዘብ ሃብት ማካበታቸውና ከቀዳሚ የአህጉሪቱ ቢሊዬነሮች ተርታ መሰለፋቸው ይነገራል፤ምንም እንኳን ኤሳቤላ ሙሰኛ በሚል መከሰሳቸውን ቢያስተባብሉም፡፡
እንደ ኤ.ኤፍ.ፒ ዘገባ ከሆነ ሩይ የእግር ኳስ መረጃዎች አጋላጩ የ’ፉትቦል ሊክስ’ መስራችም ነው፡፡ አዳዲስና በስውር የሚፈጸሙ መረጃዎችን በ’ፉትቦል ሊክስ’ በኩል በማፈትለክም ይታወቃል፡፡ የጀርመኑን ’ዴርስፒገልን’ መሰል ግዙፍ የስፖርት ጋዜጦች ከሚያወጧቸው የምርመራ ዘገባዎች ጀርባ ሩይ ነበረበት ተብሏል፡፡
ከ’ፓናማ ወረቀቶች’ ጀርባም ሩይ አለ፡፡
ዶየን የተባለውን ግዙፉ የስፖርት ኢንቨስትመንት ተቋም መረጃዎች በማጋለጡም ነበር በመረጃ ምዝበራና ስም ማጥፋት ወንጀል ከተከሰሰበት ሃንጋሪ ተላልፎ ለሃገሩ ፖርቹጋል የተሰጠው፡፡
’እጅግ ጠቃሚው አውሮፓዊ አጋላጭ’ በሚል ሩይን ያቆላመጡት የወጣቱ ጠበቃም መረጃን ከመመዝበር ይልቅ ሙስናን ጨምሮ በትልልቅ ዓለምአቀፍ ተቋማት በስውር የሚፈጸሙ ህገ ወጥ ተግባራትን ማጋለጥ መጀመሩን በመጠቆም ተከራክረዋል፡፡ፍርድ ቤቱ በነጻ እንዲያሰናብተውም ጠይቀው ነበር፡፡
ሆኖም ሩይ የተከሰሰባቸውን 90 ጉዳዮች በማየት ላይ ያለው ፍርዱ ጉዳዩ መታየቱን እንዲቀጥል ሲል አዟል፡፡