አንድ በርሜል ድፍድፍ ዘይት ትናንት በመካከለኛው ምስራቅ ከ30 ዶላር በሚበልጥ ዋጋ ተሸጧል
የነዳጅ ዋጋ እያገገመ ነው
በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት የከፋ የገበያ ችግር እና የዋጋ ቀውስ ውስጥ ገብቶ የነበረው የነዳጅ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ማንሰራራት ጀምሯል ተብሏል፡፡
እጅግ አሽቆልቁሎ ከአንድ ዶላር በታች ወርዶ የነበረው የነዳጅ ዋጋ መሻሻል ማሳየቱንም ነው አረብ ኒውስ የዘገበው፡፡
አንድ በርሜል ድፍድፍ ዘይት ትናንት በመካከለኛው ምስራቅ ከ30 ዶላር በሚበልጥ ዋጋ ሲሸጥ ነበርም ተብሏል፡፡
ይህ ችግር ውስጥ ገብቶ ከነበረበት ከያዝነው ወር አጋማሽ ወዲህ የመጀመሪያው እንደሆነም ነው ዘገባው የሚያትተው፡፡ የ13 ነጥብ 9 በመቶ ወይም የ3 ነጥብ 77 ዶላር የዋጋ ጭማሪ ስለማሳየቱም ነው የተነገረው፡፡
ከዜሮ በታች በኔጋቲቭ የዶላር ዋጋ ይሸጥ በነበረበት ምዕራባዊ ቴክሳስ የአሜሪካ ግዛት ደግሞ የ20 ነጥብ 5 በመቶ ጭማሪ አሳይቶ በ24 ነጥብ 56 ዶላር በመሸጥ ላይ ነው፡፡
በወረርሽኙ ምክንያት ነዳጅ አምራቾች የምርት ምጣኔያቸውን ቢቀንሱም አሁን አሁን ግን ፍላጎቱ እየተነቃቃ መጥቷል፡፡
ይህ ደግሞ የዋጋው መወደድን ሊያስከትል እንደሚችል የፋይናንስ ተቋማት ከወዲሁ እያሳሰቡ ይገኛሉ፡፡
የሳዑዲ የድፍድፍ ነዳጅ የውጭ ግብይት (ኤክስፖርት) በወርሃ ግንቦት በቀን ወደ ስድስት ሚሊዬን በርሜል ዝቅ እንደሚል ይጠበቃል፡፡ ይህ በኦፔክ ፕላስ አባል ሃገራት ስምምነት የሚሆን ነው ጉዳዩን ተንተን አድርገው ለሮይተርስ እንዳስረዱ ባለሙያዎች ገለጻ፡፡
በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ተጥለው የነበሩ ገደቦች መነሳት መጀመራቸው የአቅርቦትና ፍላጎትን ለማመጣጠን እንደሚያስችልም የስዊዘርላንዱ ዩ.ኤስ.ቢ ባንክ አስታውቋል፡፡
ሆኖም የፍላጎቱ ማደግና የአቅርቦቱ ማነስ ዋጋን ሊያነቃቃ ይችላል መባሉ ተስፋ ብቻ ሆኖ እንዳይቀር መስጋታቸውን የዘርፉ የገበያ ተዋናዮች አልሸሸጉም፡፡